በዞኑ ከተሞች የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

1653

ጎንደር ግንቦት 19/2010 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከተሞች የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡

በወገራ ወረዳ የገደብጌ ከተማ መሪ ማዘጋጃ ቤት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ያዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ የልማት ቴሌ ቶን ትናንት በይፋ ተጀምሯል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው በቴሌ ቶኑ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት እንደተናገሩት ከጥልቅ ተሃድሶ ማግስት ወዲህ የከተሞቹ ነዋሪዎች ያቀረቧቸውን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በተያዘው ዓመት የክልሉ መንግስት ለከተሞቹ በመደበው 17 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የከተሞቹ መሪ ማዘጋጃ ቤቶች በመደቡት 34 ሚሊዮን ብር የተለያዩ የልማት ስራዎች በህብረተሰቡ ተሳትፎ በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

እየተከናወኑ ከሚገኙ የልማት ስራዎች መካከል የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላትና የህዝብ ቤተ-መጻህፍቶች ይገኙባቸዋል፡፡

በግንባታ ወቅትም ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንደቻሉም ገልጸዋል፡፡

የወገራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ሲሳይ በበኩላቸው የቴሌ ቶኑ ዓላማ መንግስት የጀመራቸውን የልማት ስራዎች በህብረተሰቡ ተሳትፎ ጭምር ውጤታማ ለማድረግ በማሰብ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ለገደብጌ መሪ ማዘጋጃ ቤት ከተመደበው 3 ሚሊዮን ብር ውስጥ በ1 ሚሊዮን ብር ወጪ በከተማው 200 ሜትር ርዝመት ያለው የድንጋይ ንጣፍን መንገድ ተገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን ጠቁመዋል፡፡

“በከተማው የወጣቶች ችግር ሆኖ የቆየውን የእረፍት ጊዜ ማሳለፊ ቦታ ዕጦት ለመፍታት የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ለማስገንባት ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው” ብለዋል፡፡

በቴሌ ቶኑ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከአራት ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን የጠቆሙት አቶ ሳሙኤል፤ እስካሁንም ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ከህብረተሰቡ ማሰባሰብ ማቻሉን ተናግረዋል፡፡

በቴሌ ቶኑ ከተሳተፉት የከተማዋ ነዋሪ መካከል በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ማርሸት ካሴ ከሌሎች የንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ከ600 ሺህ ብር በላይ ለአካባቢው ልማት እንዲውል መለገሱን ተናግረዋል፡፡

“ሴቶችን ጨምሮ የከተማው ወጣቶች ለሚያነሱዋቸው የልማት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት በኩል የአካባቢው አስተዳደር የጀመረው ጥረት አበረታች ነው” ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ማርሸት አስማማው ናቸው፡፡

እሳቸውም የአካባቢውን ሴቶች በማስተባበርና በመቀስቀስ ለልማቱ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን ሆኖ የድርሻውን እንዲወጣ ጥረት እያደረጉ እንደሆኑም  አመልክተዋል፡፡

በቅርቡ የመሪ ማዘጋጃ ቤት ደረጃ የተሰጠውና ከተቆረቆረ 67 ዓመታት ያስቆጠረው የገደብጌ ከተማ በቁጥር ከ20 ሺህ በላይ ህዝብ እንደሚኖርበት ከወረዳው አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡