የፌደራሊዝም ስርዓት በኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገራት በተለየ መልኩ ተግባራዊ ተደርጓል--- ምህራን

107
መቀሌ ግንቦት 19/2010 ኢትዮጰያ ውስጥ የፌደራሊዝም ስርዓት ከሌሎች አገራት በተለየ መልኩ ተግባራዊ መደረጉን ምህራን ገልጹ። 27ኛ የግንቦት 20 በዓል በመቀሌ ከተማ  በፓናል ውይይትና በሙዚቃ ኮንሰርት  ተከብሯል። የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር ሐዱሽ ተስፋ በፓናል ውይይቱ ባቀረቡት ጹሁፍ ላይ እንዳሉት፣ከግንቦት20 ትላልቅ ድሎች መካከል በፌደራሊዝም የሚመራ ስርዓት እውን መሆን ነው። በዓለም በርካታ አገራት የፌደራሊዝም ስርዓት የሚከተሉ ሲሆን፣ኢትዮጰያ እውን ያደረገችው የፈደራሊዝም ስርዓት ከሌሎቹ በሁለት ዓበይት መርሆዎች ልዩ እንደሆነ አስረድቷዋል። "ኢትዮጰያ ከግንቦት 20 የድል በዓል ማግስት ጀምራ ተግባራዊ ያደረገችው የፌደራሊዝም ስርዓት በሃገሪቱ ውስጥ ያሉትን ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በእኩልነት የሚያስተዳድር ስርዓት መሆኑን ልዩ ያደርጋታል "ብለዋል። እንዲሁም የስርዓቱ ዋንኛ መሰረት ብዙሃነትን የሚያስተናግድ መሆኑንም ሁለተኛው የተለየ መልክ እንዲኖረው አድርጎታል። ስርዓቱ በህዝብ ልእልና የሚገለጽና መንግስታዊ ስልጣንን መያዝ የሚቻለው በህዝብ ድምጽ ብቻ መሆኑን ያስቀመጠ ነው ብለዋል ምሁሩ። በተጨማሪ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የባህል ልዩነቶችን በእኩልነት ያረጋገጠ ስርዓት መሆኑና መርሆዎችም በግልጽ በህገ መንግስት ማስቀመጡንም ጠቅሰዋል። ሆኖም በ27 ዓመታት የስርዓቱ ሂደት ላይ ያጋጠሙት ችግሮች እንዳሉትና ከችግሮቹ መካከልም፣በከፍተኛ የመንግስት አካላት  ሙስና፣አድልዊ አሰራር፣ለህጋዊ ስርዓት አለመገዛት እንደተዩበት አመልክተዋል። በክልሎች መካከል በራስ መንገድ የመጓዝ ፣ የህዝቦች ጥያቄዎችን በወቅቱ ምላሽ አለመስጠትና ከመጠን በላይ ያለፈ ቸልተኝነትና በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ህዝቡ ወደ ዓመጽና ግጭት እንዲያመራ መንገድ መክፈታቸውንም አስረድተዋል። የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶክተር ሐጎስ አብርሃ በበኩላቸው  የግንቦት ሃያ የድል ውጤት ከሁሉም በላይ የህዝብ ክብር የተለየ ስፍራ የሰጠ፣የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያረጋገጠ፣ባህሎቻቸውን እንዲከበሩ እውን ያደረገ መሆኑን  ገልጸዋል። የድሉ ውጤቶች አሁን አሁን እየተሸራረፉ መምጣታቸውን የተናገሩት ዶክተር ሐጎስ፣አዲሱ ትውልድ የቀድሞ አያቶቻቸውን የነጻነት ክብር ጠብቆ ውጤቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል። በፓናል ውይይቱ ላይ ከተገኙ የሰማእታት ቤተሰቦች መካከል የ88 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት አቶ ንርአ ሃይሉ ይገኙበታል። በግንቦት ሃያ የተመዘገቡ ድሎችና ለውጦችን ለማምጣት በተካሄደው የትጥቅ ትግል አራት ልጆቻቸውን መስዋእት ቢሆንም ለህዝብ ነጻነት ቤዛ በመሆናቸው የሚቆጫቸው ነው አቶ ንርአ በሰጡት አስተያየት የተናገሩት። በእሳቸውና በሌሎችም የህዝብ ልጆች የተገኙት ድሎች  አዲሱ ትውልድ መጠበቅ እንዳለበትም አመልክቷል፡፡ በፓናል ውይይቱ  ከፍተኛ አመራሮች፣ ፣የሰማእታት ቤተሰቦች፣የማህበሩ አባላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝቷል። ቀጥሎም በትግራይ የታጋይ ሰማእታት ልጆች ማህበር አስተባበሪነት የተዘጋጀውና በታዋቂ ድምጻዊያን የተሳተፉበት የሙዚቃ ኮንሰርት ተካሂዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም