በዞኑ ዝቅተኛ የነበረው ብሔራዊና ክልል አቀፍ የፈተና ውጤት ዘንድሮ ለማሻሻል ዝግጅት ተደርጓል..ጌዴኦ ዞን

104
ዲላ ግንቦት 19/2010 በጌዴኦ ዞን ባለፈው ዓመት የተመዘገበውን ዝቅተኛ ብሔራዊና ክልል አቀፍ የፈተና ውጤት ዘንድሮ ለማሻሻል  የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑ ተገለጸ፡፡ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተካልኝ ታደሰ እንዳሉት ፤ ባለፈው ዓመት ፈተናዎች ኩረጃን ለማስቀረት የተከናወነው  ስራ አበረታች ቢሆንም የተመዘገበው ውጤት አመርቂ አልነበረም። አምና ክልል አቀፍ የስምንተኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 62 በመቶ፣ 10ኛ ክፍል 17 በመቶ ወደ መሰናዶ ያለፉ ሲሆን ከ12ኛ ክፍል ደግሞ 42 በመቶው ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት በማምጣታቸው አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ሆኖ አልፏል፡፡ የመምህራን ብቃት ማነስ፣ ከተማሪ ወላጆች ጋር በቅንጅት አለመስራት እንዲሁም በቂ የቅድመ ዝግጅት ሥራና የተማሪዎች ሥነ-ልቦና ግንባታ ሥራ አለማከናወን ለውጤቱ ማነስ በዋናነት የተጠቀሱ ናቸው፡፡ በዘንድሮው  ብሔራዊና ክልል አቀፍ  ፈተናዎች አፈጻጸሙን ለማሻሻል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አቶ ተካልኝ ገልጸዋል፡፡ ከብሪቲሽ ካውንስል ጋር በመተባበር በዞኑ የሚገኙ አንድ ሺህ የሚሆኑ የእንግሊዘኛ መምህራን የብቃት ማሻሻያ ስልጠና ወስደው ለተማሪዎች የማጠናከሪያና የማካካሻ ትምህርት መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡ በሌሎች የትምህርት ዓይነቶች በብቃታቸው የላቁ መምህራንን በመመደብ የባከኑ ክፍለ ጊዜዎችን በማካካስና ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ተማሪዎቹ እንዲዘጋጁ ተደርጓል። ወላጆች ተማሪ ልጆቻቸውን እንዲከታተሉና የተሻለ ውጤት ለማምጣት በጋራ ለመስራት የምክክር መድረኮች መካሄዳቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል ፡፡ የተማሪዎችን ሥነ-ምግባርና ሥነ-ልቦና ለመገንባትና ኩረጃን ለመከላከል 467 የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር መምህራን ሥልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ማስተማር መግባታቸውን አመልክተዋል ፡፡ በፈተና ወቅት ተፈታኝ ተማሪዎችን የሚያውኩ ጉዳዮችና የስነ ምግባር ጥሰቶችን ለመከላከል በየወረዳው የፈተና ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ አጠቃላይ የፈተና ሂደቱን የመቆጣጠር ሥራ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ 1ሺህ147 የ10ኛ ክፍልና 605 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የሚያስፈትነው የዲላ መሰናዶና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል አካዳሚክ ርዕሰ መምህር ቹቹ ጎበና እንደተናገሩት፤ ከአምናው ግምገማ በመነሳት ዘንድሮ በቂ ዝግጅት ተደርጓል። ትምህርት ቤቱ ውስጥ በጥንካሬያቸው በሚታወቁና ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በትብብር በመጡ መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ተማሪዎቹን ለብሔራዊ ፈተና ሊያዘጋጁ የሚችሉ አዳዲስ ማጣቀሻ መጽሐፍትን 140 ሺህ ብር በሆነ ወጪ በመግዛት ወደ ቤተ መጻሕፍት እንዲገባ ተደርጎ አገልግሎት ላይ መዋሉንም ተናግረዋል፡፡ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ግዛቸው አለማየሁ ለብሔራዊ ፈተና በግልና በቡድን ካደረገው ዝግጅት በተጨማሪ ከመምህራኑ ባገኘው የማጠናከሪያ ትምህርት በቂ ዕውቀት መጨበጡን ገልጸዋል፡፡ " ወደ ዩኒቨርሰቲ የሚያስገባኝን በቂ ውጤት አምጥቼ የምፈልገውን የትምህርት ዓይነት ለማጥናት ተዘጋጅቻለሁ" ብሏል ተማሪ ግዛቸው፡፡ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ተካልኝ ተሰፋዬ በበኩሉ አምና ሳይማሩ ያሳለፉትን የዘጠነኛ ክፍል ምዕራፎች በማጠናከሪያ ትምህርት መሸፈን መቻላቸው በራስ መተማመናቸውን እንዳሳደገላቸው ገልፆ ጥሩ ውጤት ለማምጣት መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡ በጌዴኦ ዞን በዘንድሮው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ፈተናዎች ስምንተኛ ከፍል 15ሺህ983፣ 10ኛ ክፍል 16ሺህ177፣ እንዲሁም 12ኛ ክፍል 1ሺህ667 ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀርቡ የዞኑ ትምህርት መምሪያ አመልክቷል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም