የመከላከያ ሰራዊት ቀንን አስመልክቶ የሰራዊቱ አባላት በድሬዳዋ የጽዳት ዘመቻ አካሔዱ

112

ድሬዳዋ ጥር 19/2011 ድሬዳዋን ጽዱ ውብና ሰላሟ የተጠበቀ ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት ሁሉ የመላከያ ሰራዊት ግንባር ቀደም በመሆን እንደሚሰራ የምስራቅ ዕዝ ሆስፒታል አስተባባሪ ኮሎኔል ጌታቸው መሀመድ ተናገሩ።

የሰራዊቱን ቀን ምክንያት በማድረግ ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ በተከናወነ የጽዳት ዘመቻ በሺህ የሚቆጠሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የአስተዳደሩና የፊደራል ፖሊስ አባላት ተሳትፈዋል።

በዘመቻው በዚህ ሳምንት ከወጣቶች ሰልፍና ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ በጎማ ቃጠሎ የቆሸሹ ዋና ዋና ጎዳናዎች መጽዳት ችለዋል፡፡   

ሌተናል ኮሎኔል ጌታቸው መሀመድ የምስራቅ ዕዝ ሆስፒታል የፋርማሲ ዳይግኖስቲክ አስተባባሪ በመጪው የካቲት 7 የሚከበረውን የመከላከያ ሰራዊት ቀን ምክንያት በማድረግ የሰራዊቱ አባላት ድሬደዋን ጽዱ የማድረግ ስራ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

''የህብረተሰቡ አንድ አካል ነን፤የነዋሪዉን ማህበራዊ ችግር ለመፍታት በሚከናወኑ ተግባራት ግንባር ቀደም ሆነን  እየሰራን ነው" ብለዋል።  

"ከጽዳት ዘመቻ ባሻገር የፈረሱ የአዛውንት  ቤቶችን በመጠገን እና በማደስ አርያነቱን እያስመሰከረ ይገኛል" ያሉት ደግሞ ሻለቃ ተፈራ ማርቆስ ናቸው።                                                                                               

"ሰራዊቱ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን ከመጠበቅ በተጨማሪ ከድሬዳዋ ህብረተሰብ ጋር በመተባበር የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ያደርጋል" ብለዋል፡፡ 

የሰራዊት ቀንን በፅዳት፣ በልማታዊ እንቅስቃሴ፤ ከህብረተሰቡ ጋር  ትስስሩን በሚያጠናክሩ ውይይቶችና በሌሎች ተግባራት እንደሚያከብሩ የገለፁት ደግሞ አስር አለቃ ዘውገ ግርማ ናቸው፡፡

የድሬዳዋን ፅዳትና ውበት ለመመለስ በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብ ተሳትፎና እገዛ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምስራቅ ዕዝ የደረጃ ሶስት ሆስፒታል ዳይሬክተር ካቦ ሁሴን "መከላከልን መሰረት ያደረገው የጤና ፖሊሲን ዕውን ማድረግ የሚጀመረው ቁሻሻን በተባበረ ክንድ በዘላቂነት በማፅዳት ጭምር ነው" ብለዋል፡፡

አስተዳደሩ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ለከተማይቱ ጽዳትና ውበት መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በፅዳት ዘመቻው ላይ የድሬዳዋ ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማንና የካቢኔ አባላት እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት አዛዦች ተካፋይ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም