በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች እየተዘዋወርኩ ስለ ሰላም በማስተማር ድርሻዬን እወጣለሁ - ባለ ራዕዩ ኤልሳ ቱሪ

93

አዲስ አበባ ጥር 18/2011 በኢትዮጵያ ሰባት ከተሞች በመዘዋወር በየአደባባዮች ስለ ሰላም በማስተማር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ራሳቸውን ''ባለ ራዕዩ ኤልሳ ቱሪ'' በማለት የሚጠሩ ግለሰብ ተናገሩ።

ነዋሪነታቸው በኔዘርላንድስ የሆኑት አቶ ኤልሳ ቱሪ ለ30 አመታት በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ ካናዳና ሌሎች አገሮች በመዘዋወር ስለ ሰላም ሲሰብኩ እንደኖሩ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በቅርብ ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ ከተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ተወግደው በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ንቅናቄ ለመፍጠር ዕቅድ ይዘው ለመስራት ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል።

አቶ ኤልሳ እንደገለጹት፤ ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ፣ ነቀምት፣ አዳማ፣ ባህርዳር፣ መቀሌ፣ ሀዋሳና ጎንደር ከተሞች በመዘዋወር ሕብረተሰቡ ሰከን ባለ ሁኔታ በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየትን የዘወትር ልምዱ ካደረገ የሚፈለገው ውጤት ማግኘት እንደሚችል ያስተምራሉ።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ድርጊቶችን ለማስቆም የመንግስት አካላት፣ የሀይማኖት አባቶችና ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

ከፌደራልና ከክልል ባለ ድርሻ አካላት ጋርም በጋራ ለመስራት ማቀዳቸውን አክለዋል።

አቶ ኤልሳ እንደገለጹት፤ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው ግጭት ለማስቆም የተከናወነውን ዕርቅ የሚያደስትና መጠናከር ያለበት ድርጊት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም