ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ጤናና አያያዝ ላይ ለአርብቶ አደሮች ስልጠና እየሰጠ ነው

89

ጋምቤላ ጥር 18/2011 ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ  በአራት ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ አርብቶ አደሮች በእንስሳት ጤናና አያያዝ ላይ ያተኮረ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በጋምቤላ ክልል ላሬ ወረዳ ከ150 እስከ 350 የቀንድ ከብቶች ላሏቸው አርብቶ አደሮች ለሦስት ቀን የሰጠው ስልጠና ተጠናቋል ።

በዩኒቨርሲቲው የማህብረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ሩድ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በክልሉ ያለውን ሰፊ የእንስሳት ሀብት በምርምር በማገዝ የአካባቢውን አርብቶ አደር ከእንስሳቱ የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው።

በተጨማሪም በክልሉ በሚገኙ አራት ወረዳዎች በእንስሳት ጤና፣ እርባታና አያያዝ ላይ ለአርብቶ አደሮችና ለባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል ።

በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት እርባታና ጤና ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጀንበሩ አለሙ በበኩላቸው በክልሉ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ቢኖርም በተሻሻለ ዘዴ ባለመያዙ  አርብቶ አደሩ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመለየትና ዘርፉን በምርምር በማገዝ  የአርብቶ አደሩን ህይወት ለማሻሸል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዶክተር ጀንበሩ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ባህላዊና ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ዘዴዎችን በማቀናጀት ለአርብቶ አደሩ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።

"ከመኖ ጋር ተያይዞ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሉ ምርምሮች ለማካሄድም እየተሰራ ነው" ሲሉም ገልጸዋል ።

ስልጠናው የተሰጣቸው አርብቶ አደሮች በበኩላቸው ያገኙት ግንዛቤ ለከብቶቻቸው አያያዝና ጤና ትኩረት እንዲሰጡ የሚያግዛቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

ከስልጠና ተሳታፊዎች ማካከል አርብቶ አደር ፒተር ሉዋል ለኢዜአ እንዳሉት የከብቶቻቸው ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም በመኖና እንስሳት አያያዝ ችግር ምክንያት የሚያገኙት ጥቅም ዝቅተኛ ነው፡፡

"ብዙ ከብቶች ቢኖሩንም የምንጠቀመው ባህላዊ የአረባብ ዘዴ በመሆኑ ተጠቃሚ ልንሆን አልቻልንም፤ ዩኒቨርሲቲው የሰጠን ስልጠና በቀጣይ ከብቶቻችንን እንዴት መያዝና የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንዳለብን ያግዘናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም