ባህላዊ የመሬት ውስጥ ጎተራ ሰብልን ከተባይና ከብክነት ለመታደግ እያገለገለ ነው-የደራሼ ማህበረሰብ አባላት

76

አርባምንጭ ጥር 18/2011 " ፖሎት" የተሰኘ የተደራሼ ባህላዊ የመሬት ውስጥ የምርትን ማከማቻ  ከብክነትንና ተባይን በመታደግ ለረጅም ጊዜ ለማቆየት እየረዳቸው መሆኑን የማህበረሰቡ አባላት ገለፁ።

ባህላዊ ጎተራው ምርትን ከድንገተኛ እሳት ቃጠሎ አደጋ ለመታደግ አማራጭ እንደሆነም ተናግሯል።

በወረዳው የአተያ ቀበሌ አርሶአደር ካርቶ ከበደ ለኢዜአ  እንዳሉት  ጎተራው ሰብል በተባይ ሳይበላና ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ ያደርጋል፡፡

"መሬት ተቆፍሮ የተሰራ በመሆኑና ስፍራው ከባለቤቱ ውጪ በቀላሉ ስለማይታወቅ እህላችን በሌባ እንዳይሰረቅ በማድረግ ጠቅሞናል " ብለዋል ።

"ጎተራው ጠቃሚ ቅርስ በመሆኑ በአግባቡ ተጠብቆ ለልጆቼ ይተላለፋል" ያሉት አርሶአደር ካርቶ ሁለት ጎተራ እንዳላቸው ተናግረዋል ።

አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ የሰብል እጥረትና ድርቅ በሚከሰትበት ጊዜ በጎተራው ያከማቹት የምግብ እህል እየጠቀማቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ በወረዳው የግራሼ ቀበሌ አርሶ አደር ጌታቸው ገለንጮ ናቸው፡፡

እንደ አርሶ አደር ጌታቸው ገለጻ በጎተራው የሚጠራቀመው እህል በተባይ ስለማይበላ በቁጠባ እንዲጠቀሙ አስችላቸዋል ።

የደራሼ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ሙዳ "ባህላዊውን የመሬት ውስጥ ጎተራ የወረዳው አርሶአደሮች ከጥንት ጀምሮ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል" ብለዋል ።

ጎተራው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የተናገሩት  ኃላፊው የአገዳ ሰብሎችን በተባይ ሳይበሉ ለረጅም ጊዜ የሚያቆይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ጎተራው በባህሪው በቆሎ፣ማሽላና መሰል የአገዳ ሰብሎችን ብቻ ለማከማቸት የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል ።

"አርሶ አደሩ ሰብልን ለረዝም ጊዜ በማቆየት ለችግር ጊዜ ለመጠቀም አስቦ የተሰራ በመሆኑ የማህበረሰቡ የቁጠባ ባህሉም እንዲጎለብት አስተዋጽኦ አድርጓል " ብለዋል ።

"አርሶ አደሮች የደረሱ የአገዳ ሰብሎችን ከሰበሰቡ በኋላ በጋራ በመፈልፈል በጎተራው ያጠራቅማሉ" ሲሉም ተናግረዋል ።

ባህላዊ የመሬት ውስጥ ጎተራው ከ2 እስከ 3 ሜትር ጥልቀትና ከ3 እስከ 4 ሜትር ስፋት ያለው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ በወረዳው 27ሺ 400 የሚጠጉ አርሶ አደሮች  በነብስ ወከፍ እሰከ አምስት ጎተራ አላቸው፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህል ተመራማሪ አቶ ፍሬው ተስፋዬ ባህላዊ የከርሰ ምድር ጎተራው በሌሎች አከባቢዎች ያልተለመደ የደራሼዎች ባህላዊ ቅርስ መሆኑን ጠቁመዋል ።

"በማህበረሰቡ አገር በቀል እውቀት የተሰራው ጎተራ በጣሊያን ወረራ ወቅት እህልን ከውድመት መታደጉን ተከትሎ በስፋት ጥቅም ላይ ሊውል ችሏል " ብለዋል ።

በአከባቢው በርካታ  ባህላዊና ታሪክዊ መስህቦች መኖራቸውን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ክልል ባህልና ቱርዝም ቢሮ የባህልና ታሪክ  ዳይሬክተር አቶ መልካሙ ጋጋዶ ናቸው፡፡

"ጎተራው የማህበረሰቡ አባላት ሰብል በተባይ ሳይበላ  ለረጅም ጊዜ የሚያቆዩበት ብቻ ሳይሆን በድንገተኛ ቃጠሎ ክስተት ወቅት  ንብረታቸውን ከውደመት የሚታደጉበት ነው" ብለዋል ።

ባህላዊ ጎተራውን  በጥናት በማስደገፍ ለዓለም አቀፍ መድረኮች ለማስተዋወቅ ጥረት እንደሚደረግም አመልክተዋል።

" ፖሎት"  የተሰኘው የደራሼ ማህበረሰብ መገለጫ የሆነው ባህላዊ ጎተራ በአንድ ጊዜ ከ100 ኩንታል በላይ የሰብል ምርት በመያዝ  ሳይበላሽ እስከ 40 ዓመት ማቆየት  እንደሚችል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም