የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳል

54

አዲስ አበባ  ጥር 17/2011 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከአምናው የሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ከረፋዱ 4 ሰአት ከ 30 ደቂቃ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከፌደራል ፖሊስ ጋር ይጫወታሉ።

ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ከጠዋቱ ሶስት ላይ ይጫወታሉ።

ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ ሶስት ሰአት መከላከያ ከአዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ቡድን ከሆነው ጎንደር ከተማ ጋር ይጫወታል።

ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከከምባታ ዱራሜ ከጠዋቱ ሶስት ላይ የሚጫወቱ ይሆናል።

በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 10 የእጅ ኳስ ቡድኖች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ፕሪሚየር ሊጉ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን፤ መከላከያ የ2009 ዓ.ም፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደግሞ የ2010 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊዎች መሆናቸው ይታወሳል።

በሌላ በኩል በሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በስድስተኛ ሳምንት አንድ ጨዋታ የሚካሄድ ሲሆን መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ በሜዳው ጣና ባህርዳርን ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ላይ ያስተናግዳል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በመደወላቡ ዩኒቨርስቲ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የስፖርት ጉባኤ ላይ የቮሊቦል ቡድኖች እየተሳተፉ በመሆኑ የስድስተኛ ሳምንት አንድ ጨዋታ ብቻ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታውቋል።

መዳወላቡ ዩኒቨርስቲ ከጣና ባህርዳር ጨዋታው የሚካሄደው የስፖርቱን እንቅስቃሴ ለጉባኤው ታዳሚ ለማሳየት እንደሆነም ተመልክቷል።

አዲስ አበባ ፖሊስ ከመከላከያ፣ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከወላይታ ድቻና ሙገር ሲሚንቶ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ጋር ሊያደርጓቸው የነበሩ የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ለሌላ ጊዜ ተራዝመዋል።

በሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ስምንት ቡድኖች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም