የተገኙ ድሎች ይበልጥ እንዲያብቡ አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል --ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ

91
አዳማ ግንቦት 19/2010 በግንቦት 20 የተገኙ ድሎች ይበልጥ እንዲያብቡ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ አሳሰቡ። 27ኛው የግንቦት 20 በዓል በክልል ደረጃ ዛሬ በአዳማ ገልማ አባገዳ የስብሰባ ማዕከል በፓናል ውይይት ተከብሯል። በዚህ ወቅት ፕሬዝዳንት ለማ እንደገለጹት  የግንቦት 20 ድል በሀገሪቱ የለውጥ ጎዳና የተጀመረበት፣ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ እድገት መሰረት የተጣለበት ቀን ነው። "በዓሉን ስናከብር ያለፉትን ስርዓቶች ለማውገዝና ለማጣጣል ሳይሆን ተጨማሪ ድል ለማስመዝገብ በአዲስ መንፈስ የምንነሳሳበት ሊሆን ይገባል" ብለዋል። አንድነትን የሚሸረሽሩ አስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን በማስወገድ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን ለተጨማሪ የልማት ስኬቶችና ሀገራዊ ብልጽግና በአንድነት መሰለፍ ያስፈልጋል። እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ፌዴራሊዝም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነታቸው ተከብሮላቸው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በማስቻሉ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲፈጥሩ በር ከፍቷል። የኦሮሚያ ክልል መንግስት በቀጣይ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ እኩልነትና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት መረጋገጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ህዝቡ በባለቤትነት መንፈስ ተሳትፎውን ሊያጠናክር እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የክልሉን መንግስት የሚመራው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በጥልቅ ተሃድሶ ባደረገው ያላሰለሳ ትግል ሀገሪቱን ከመበታተን አደጋ መታደጉን አቶ ለማ ገልጸዋል። ላጋጠሙት  ተግዳሮቶች ሁሉ የፌዴራላዊ ሥርዓት መፍትሄዎችን ማምጣቱን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ "በቀጣይም የሚያጋጥሙን ችግሮች በተመሳሳይ መልኩ እየፈታን መሄዳችንን እንቀጥላለን"ብለዋል። በዓሉ የሚከበረው ባለፉት ዓመታት ካጋጠሙ ተግዳሮት በመማር፣ ክፍተቶችን ለማረምና ተጨማሪ ድል ለማስመዝገብ በመዘጋጀት እንደሆነም ተናግረዋል። የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ በበኩላቸው ግንቦት 20 በህዝብ ላይ ለዘመናት ተጭኖ የቆየውን አፈናና ጭቆና በማስቀረት የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ያደረገ ልዩ ቀን መሆኑን  ገልጸዋል። የፌዴራል ሥርዓቱ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የክልሉ ህዝብ ባህሉን፣ ቋንቋውንና ታሪኩን ማሳደግና ማበልጸግ መቻሉንም ተናግረዋል። ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አባገዳ በየነ ሰንበቶ በሰጡት አስተያየት፤ 'የግንቦት 20 ድል የክልሉንም ሆነ የሀገሪቱን ህዝቦች ከጨቋኝ ስርዓት አላቆ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም በማስፈን እኩል የመልማት መብታቸውን እንዲጠቀሙ ማድረጉን ተናግረዋል። ሀገራዊ ሰላም የማስጠበቅና የልማት ስራዎችን የማስቀጠል ተግባር ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅ በመሆኑ አስፈላጊውን ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል አባገዳ በየነ። ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ ካሰች አመንቴ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩት ምቹ ሁኔታዎች ሴት ልጅ መስራት እንደምትችል በተግባር በማሳየት የመብቷ ተጠቃሚ መሆን እንደቻለች ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ባስገኘው ውጤት ዙሪያ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በበዓሉ አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ከክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም