ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በሱማሌ ክልል በተፈጸሙ ወንጀሎች የደረሰበትን የምርመራ ግኝት ይፋ አደረገ

86

አዲስ አበባ ጥር 17/2011 ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በሱማሌ ክልል በተፈፀሙ ወንጀሎች ላይ በምርመራ የደረሰባቸውን ግኝቶች ይፋ አደረገ።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሱማሌ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ ህገ-መንግስታዊ ስርዓትን ለመናድ በመንቀሳቀስ ንብረት እንዲወድምና በተያያዥ ወንጀሎች 46 ያህል ተጠርጣሪዎች ተለይተዋል።

የምርመራ ስራው በዋናነት የክልሉን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጨምሮ 46 ሰዎችን በማካተት እንደተከናወነ ተጠቅሶ በስድስቱ ላይ ክስ እንደተመሰረተ ተገልጿል።

40 ዎቹ ደግሞ በሂደት ተይዘው ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።

ከአገር የወጡ ባለስልጣናትን ወደ አገር በመመለስ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከተሸሸጉባቸው አገሮች ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንና በአገር ቤት የተደበቁትንም በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች ያለመከሰስ መብት ያላቸው በመሆኑ መብታቸውን በማንሳት በቁጥጥር ስር ለማዋል ስራዎች እየተሰሩ ነው ተብሏል።

በክልሉ ከተገኘ የጅምላ መቃብር የተቀበሩ 200 ግለሰቦች ውስጥ የ37ቱ አስከሬን መውጣቱ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪ 266 የሚደርሱ ሰዎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል።

በክልሉ 'ሂጎ' በሚል ስም የተደራጀ ቡድን እና የተወሰኑ የክልሉ የልዩ ፖሊስ አባላት አማካኝነት በ10 ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ድርጊት መፈጸሙንና ማንነታቸው ባልተገለጹ በርካታ ሴቶች ላይ ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙ በምርመራ መለየቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የመንግስትንና የግለሰብ መኖሪያና ንግድ ቤቶች ላይ በደረሰ አደጋ 412 ሚሊዮን 468ሺህ 826 ብር የሚገመት ንብረት መውደሙ መታወቁንም ተናግረዋል።

በርካታ ዜጎችም ከመኖሪያ ቤታቸው እንዲፈናቀሉና ተገድለው በጅምላ እንዲቀበሩ ተደርገዋል።

ከሀምሌ 28 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የተፈፀመው ወንጀል ውስብስብና አስቸጋሪ በመሆኑ የምርመራ ሂደቱ አምስት ወር ሊወስድ እንደቻለም አቶ ዝናቡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም