የደንጉ ትኩሳት ወረርሽኝ ሱማሌ ክልል መከሰቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ

98

አዲስ አበባ  ጥር 17/2011 በሱማሌ ክልል ፊቅ ዞን ለገሂዳ ወረዳ የደንጉ ትኩሳት ወረርሽኝ ከሰባት ቀናት በፊት መከሰቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የደንጉ ትኩሳት ወረርሽኝ በክልሉ ከሰባት ወራት በፊት በዶሎ አዶ ወረዳ ተከስቶ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በለገ ሂዳ ወረዳ ተከስቷል፡፡

በወረርሽኙ 60 ሰዎች መጠቃታቸውን ከተያዙት 60 ሰዎች ውስጥ 41ዱ ህፃናት ሲሆኑ 19ኙ ደግሞ አዋቂዎች ናቸው ብለዋል። 

የክልሉ ፈጣን የህክምና ምላሽ ሰጪ ቡድን በወረርሽኙ ለተጠቁ ሰዎች የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ወረርሽኙ በምን ምክንያት እንደተነሳ ፈጣን የዳሰሳ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፈጣን የህክምና ምላሽ ሰጪ ቡድን ለተጨማሪ እገዛና ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ወደ አካባቢው መላኩንም ገልጸዋል። 

በወረርሽኙ በተጠቁ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ራስ ምታት፣ ነስር፣ የሰውነት ላይ ሽፍታ፣ ከዓይን ጀርባ ከፍተኛ ህመም፣ በጡንቻና በመገጣጠሚያዎች ላይ ህመም፣ ማቅለሽለሽና ማስታወክ ምልክት እንደታየባቸውም ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በአካባቢው የተከሰተው ወረርሽኝ የደንጉ ትኩሳት መሆኑን ለማረጋገጥ የደም ናሙና ወስዶ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር በየነ፤ ለተጨማሪ ምርመራ የደም ናሙናው በቅርቡ ወደ ሲኔጋል ዳካር ወይም ኡጋንዳ እንደሚላክም ገልጸዋል። 

እንደ ዶክተር በየነ ገለጻ በጥቂት ሰዎች ላይ በተለየ ሁኔታ አደገኛ የደንጉ ትኩሳት ምልክቶች የሚታይባቸው ሲሆን ከ3 እስከ 7 ቀን ድረስ ደም የቀላቀለ የማያቋርጥ ትውከት፣ ከፍተኛ የሆድ ህመም፣ ወደላይ መተንፈስና የድድ መድማት አጋጥማቸዋል።

እንዲህ ዓይነት ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች ከ24 እስከ 48 ሰዓት ድረስ ህክምና ካላገኘ ለህልፈተ ህይወት ሊዳረግ እንደሚችልም ገልጸዋል።

በሽታው የሚከሰተው ''ኤደስ'' በተባለ የወባ ትንኝ አማካይነት ሲሆን በተለይ ቀን ላይ የመናከስ ባህርይ እንዳላቸው የገለጹት ዶክተር በየነ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ሙሉ ሰውነታቸውን የሚሸፍን ልብስ እንዲለብሱም መክረዋል።

በበሽታው ተይዞ የዳነ ሰው ቫይረሱ በሰውነቱ ውስጥ ተደብቆ የሚኖር ሲሆን ቆይቶም ቢሆን ቫይረሱን ወደ ጤነኛ ሰው እንደሚያስተላለፍም አስረድተዋል።

በተያዘው ዓመት የለገ ሂዳ ወረዳን ጨምሮ በክልሉ 331 ሰዎች ላይ የደንጉ ትኩሳት ምልክት መታየቱን ገልጸዋል።

ለደንጉ ተጋላጭ የሆኑና የደንጉ በሽታ ይኖርባቸዋል ተብሎ በሚታሰቡ አካባቢዎች  አሁን በሽታው የተከሰተባቸውን ጨምሮ የቅኝት ስራዎች እንደሚሰራም ዶክተር በየነ አክለው ገልጸዋል።

የደንጉ ትኩሳት ወረርሽኝ ከ2005 እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ በድሬደዋ እንዲሁም ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ በሱማሌ ክልል ጎዴና በቀብሪደሃር ዞኖች ተከስቶ እንደነበረም አብራርተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ግማሽ ያህሉ ህዝብ ለደንጉ ትኩሳት ወረርሽኝ ተጋለጭ ሲሆን በዓለም የጤና ድርጅት ግምት መሰረት በየዓመቱ 390 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው ይያዛሉ ከእነዚህም ወስጥ 96 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ምልክቱ ብቻ የሚታይባቸው እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም