ምርታቸውን በማህበራት በኩል ለገበያ ማቅረባቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በታህታይ አዲያቦ የሰሊጥ አማራቾች ገለጹ

67

ሽሬ ጥር 17/2011ምርታቸውን በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል ለገበያ ማቅረብ በመጀመራቸው ተጠቃሚ  እንዳደረጋቸው  በትግራይ ክልል  ታህታይ አዲያቦ ወረዳ የሰሊጥ አማራቾች ገለጹ።

አምራቾቹ ለኢዜአ እንዳሉት ላመረቱት ሰሊጥ  የሚሸጡበት የገበያ  ትስስር በመፈጠሩ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡

በወረዳው የገምሃሎ የገጠር ቀበሌ  አርሶ አደር ተክለማርያም ሃጎስ ከአሁን በፊት የሰሊጥ ምርታቸው የገበያ አገናኝ ነን በሚሉ ግለሰቦች በኩል ያቀርቡ በነበረበት ወቅት  ተጠቃሚ እንደልሆኑ ተናግረዋል።

በ2010/2011 የምርት ወቅት ያመረቱትን ሃያ ኩንታል ሰለጥ  በህብረት ሥራ ማህበር በኩል ለገበያ አቅርበው  ከ108 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ክሕሽን ገብረመድህን በበኩላቸው ቀደም ሲል በደላሎች በኩል ምርታቸን በተጭበረበረ ዋጋ ይሸጥ እንደነበረና በዚህም  የድካማቸውን ያህል ሳያገኙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው  የህብረት ሥራ ማህበር በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ  ምርታቸውን  ለገበያ ማቅረብ በመጀመራቸው  በተሻለ ዋጋ መሽጥ እንደቻሉ አስረድተዋል።

ባለፈው የመኸር ወቅት ካመረቱት ሰለጥ 94 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

በህብረት ሥራ ማህበር በኩል በተሻለ ዋጋ ከተሸጠው 13 ኩንታል  የሰለጥ ምርት 61 ሺህ 425 ብር ገቢ ማግኘታቸው  የተናገሩት ደግሞ በወረዳው የለምለም  ቀበሌ  አርሶ አደር ግርማይ ሸጊ ናቸው፡፡

በወረዳው የፍረ ቃልሲ ሁለገብ የህብረት ሥራ ማህበር አስተባባሪ አቶ በላይ ምትኩ እንደገለጹት  የሰሊጥ አምራች አርሶ አደሮችን ምርት በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ ማድረግ ተጀምሯል።

አምራቾቹ የድካማቸው ዋጋ ማግኘት በመጀመራቸው የሰሊጥ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ  መነሳሳት መፍጠሩን  አመልክተዋል።

በወረዳው  ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት የሰብል ባለሙያ  አቶ ሙሉብርሀን አብረሀ  በወረዳው ባለፈው የመኸር ወቅት በተለያየ የሰብል ዘር  ከተሸፈነው 67 ሺህ 800 ሄክታር ማሳ ውስጥ  25 ሺህ 785 ሄክታሩ በሰሊጥ የለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሰሊጥ ከተሸፈነ መሬት ከ174 ሺህ ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርት መሰብሰቡን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም