በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ100 ቀናት እቅድ ያለአግባብ የማይፈጽሙ ተቋማት ይጠየቃሉ---አቶ አሻድ ሃሰን

74

አሶሳ ጥር 17/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለህብረተሰቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀው የ100 ቀናት እቅድ በተለመዱ ምክንያቶች የማይፈጽሙ ተቋማትን ተጠያቂ እንደሚሆኑ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  አቶ አሻድ ሃሰን  አስታወቁ፡፡

እቅዱ ትናንት ማምሻውን ይፋ ሲደረግ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ 14 መስሪያ ቤቶችና ተቋማት የ100 ቀናት እቅድ አዘጋጅተዋል፡፡

"እቅዱ  የህብረተሰቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በሚያስችል መልክ ለማዘጋጀት ጥረት ተደርጓል "ብለዋል፡፡

የየመስሪያ ቤቱና የተቋማት ስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በእቅዳቸው ላይ እየተወያዩ እንደሆነ ጠቁመው ለአፈጻጸሙ እንደሚፈራረሙ ተናግረዋል፡፡

"እቅድ ካልተፈጸመ ዋጋ የለውም" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ከዚህ ቀደም ለእቅድ አፈጻጸም ማነስ በስፋት ሲነሱ የነበሩ የተለመዱ የማስፈጸም አቅም ማነስና ሌሎችም ምክንያቶችን መጥቀስ ተቀባይነት እንደማይኖረው አስረድተዋል፡፡

እያንዳንዱ የክልሉ ተቋም ያለው በጀት እና የሠው ኃይል እንደሚታወቅ ያመለከቱት አቶ አሻድሊ ተቋማት ይህንን መሠረት በማድረግ እቅዳቸውን መፈጸም እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

እቅዳቸውን ለማሳካት አቅማቸውን አሟጠው የሚሰሩ የተሻለ አፈጻጸም ከማስመዝገብ የሚያግዳቸው እንደሌለ ተናግረው በዚህ ሂደት  ችግር የሚያጋጥማቸውን ተቋማት መስተዳድሩ አስፈላጊ እገዛ እንደሚደረግ  አመልክተዋል፡፡

ሆኖም በትኩረት ማነስና ሌሎችም ድክመቶች እቅዳቸውን ተፈጻሚ የማያደርጉ ተቋማትን የክልሉ መንግስት በመጠየቅ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚውስድ አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት፣ ግብርና እና ጤና ቢሮዎች የተጠቃለለ  የ100 ቀናት እቅዳቸውን በዚሁ ወቅት ያቀረቡ ሲሆን ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የክልሉ የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ቴሶ በበኩላቸው " የክልሉን ህዝብ ቁጥር ጨምሮ የሥራ አጦችን ትክክለኛ ቁጥር የሚመለከት መረጃ የለም" ብለዋል፡፡

በዚህም ሳቢያ የእርሳቸው ቢሮ ባለፉት ዓመታት ግምታዊ መረጃዎችን መሠረት ያደረጉ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

በጥናት የተደገፈ መረጃ አለመኖር በእቅድ አዘገጃጀት እና አፈጻጸም እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

" እቅዱ ከተለመደ አሰራር እንድንወጣ ያስገድደናል" ያሉት ደግሞ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አካሻ እስማኤል ናቸው፡፡

ስኬታማ መሆን የሚቻለው  ተጨባጭ እቅዶች ሲያዘጋጁ እንደሆነ አመልክተው የሁሉም ተቋም አመራርና ሠራተኛ ወጥ የሆነ የእቅድ አዘገጃጀትና የአፈጻጸም መለኪያ ሊቀመጥላቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ይህም የሠሩትን ለማወደስና ያልሰሩትን ለመጠየቅ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ የለውጥ እና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው  ፊሊጶስ የ100 ቀናት እቅዶቹ የተዘጋጁት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ መሠረት ያደረጉ እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

በዚሁ ውይይት የክልሉ የተለያዩ መስሪያ ቤቶችና ተቋማት ኃላፊዎችና  የስራ ሂደት ባለቤቶች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም