በኦሮሚያ በመጀመረያው ዙር በመስኖ ከለማው መሬት 124 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰበሰበ

57
አዳማ ግንቦት 19/2010 በኦሮሚያ ክልል በተያዘው ዓመት የመጀመሪያ ዙር በመስኖ ከለማው መሬት 124 ሚለዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡ ተገለጸ፡፡ በሁለተኛው ዙር 79 ሚለዮን ኩንታል ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል። የኦሮሚያ መስኖ ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰይፈዲን መሀዲን እንዳስታወቁት የተሰበሰበው ምርት በመስኖ ከለማው 986 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ነው፡፡ የተመረተውም የአትክልት፣ የስራስርና የበቆሎ ሰብል እንደሆነ አመልክተዋል። በሁለተኛው ዙር ደግሞ 700 ሺህ ሔክታር ለማልማት ታቅዶ እስከ አሁን ግማሽ ሚሊዮን ሔክታር መሬት በዘር መሸፈኑንና ቀሪውን ለመተግበር እየተሰራ መሆኑ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ከዚህም 79 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል። በኦሮሚያ ክልል ለመስኖ ልማት አመቺ የሆነ መሬትና የውሃ ሀብት መኖሩን የገለፁት አቶ ሰይፈዲን  የጃፓን አለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ)  ዘርፉን በቴክኒክ፣ በቁሳቁስና  በልምድ ልውውጥ እያገዘው መሆኑን አስረድተዋል። ጃይካ በክልሉ የመስኖ ፍኖተ ካርታ ከማዘጋጀት አንስቶ በአራት ዞኖች አምስት የመስኖ ልማት ግንባታዎች ማካሄዱንና ለመስኖ ልማት የሚያገለግሉ 14 መመሪያዎችን አዘጋጅቶ ማስረከቡን ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። ጃይካ ለክልሉ የሚያደርገውን ድጋፍ በመገምገም ቀጣይነቱን ለማጠናከር ያለመ የምክክር መድረክ  በአዳማ ከተማ ተካሔዷል። በመድረኩ የተገኙት በግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የአነስተኛ መስኖ ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ አወል በበኩላቸው መንግስት ለአርሶ አደሮች የውሃ አማራጮችን በማስፋት የመስኖ ልማት ተጠቃሚታቸውን እንዲያረጋግጡ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዘርፉ ሰፊ ሀብት የሚጠይቅና ከአደረጃጀት አንስቶ የአቅም ችግር የሚታይበት በመሆኑ የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ገና ብዙ መስራት እንደሚጠይቅም ገልጸዋል። ጃይካና ሌሎች አጋር ተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍ ዘርፉን ለማሻሻል ለሚደረገው ጥረት አስተዋፅኦው የማይናቅ መሆኑንም ጠቁመዋል። በጃይካ የኢትዮጵያ ዋና ተጠሪ ሚስተር ኬን ያማዳ በሰጡት አስተያየት "የጃፓን መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር የሚያደርገውን የልማት ትብብር በግብርናው፣ በኢንዱስትሪ፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል። በኦሮሚያ ክልል በመስኖ ሊለማ የሚችል አንድ ሚሊዮን 300ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚገኝ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም