በዱባይ ማራቶን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል

87

አዲስ አበባ ጥር 17/2011 ዛሬ ማለዳ በተካሄደው የዱባይ ማራቶን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ በመግባት አሸነፉ።

በውድድሩ አትሌት ጌታነህ ሞላ 2 ሠዓት ከ3 ደቂቃ ከ34 ሴኮንድ በመግባት በአንደኝነት አሸንፏል።

አትሌቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካፈለበት ውድድር የቦታውን ክብረ ወሰን በ26 ሴኮንድ አሻሽሏል።

የቦታው ክብረወሰን በአትሌት ሞስነት ገረመው 2 ሠአት ከ4 ደቂቃ ከ00 ሴኮንድ ተይዞ ነበረ ሲሆን በወቅቱ አትሌቱ የገባበት ሠዓት በማራቶን ታሪክ የመጀመሪያው ፈጣን ሠዓት ሆኖ ተመዝግቦ ነበር።

በዛሬው ውድድር አትሌት ሄርጳሳ ነጋሳ 2 ሠዓት ከ3 ደቂቃ ከ40 ሴኮንድ በመግባት 2ኛ፣ አትሌት አሰፋ መንግስቱ 2 ሠዓት ከ4 ደቂቃ ከ24 ሴኮንድ በመግባት ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል።

የዚህ ውድድር ከ5ኛ እስከ 9ኛ ድረስ ያለውም ደረጃ በኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ነው የተያዘው።

በሴቶች ማራቶን ኬንያዊቷ አትሌት ሩት ቼፕጌቲች 2 ሠዓት ከ17 ደቂቃ ከ7 ሴኮንድ በመግባት አሸንፋለች።

አትሌት ቼፕጌቲች የገባችበት ሠዓት በሴቶች ማራቶን ታሪክ ከእንግሊዛዊቷ አትሌት ፓውላ ራድክሊፍና ከኬንያዊቷ አትሌት ማሪ ኬይታኒ በመቀጠል ሦስተኛው ፈጣን ሠዓት ሆኖ ተመዝግቧል።

ባለፈው ዓመት የዱባይ ማራቶን አትሌት ሮዛ ደረጀ 2 ሠዓት ከ19 ደቂቃ ከ17 ሴኮንድ በመግባት ይዛው የነበረውን የቦታውን ክብረ ወሰን አትሌት ቼፕጌቲች በ2 ደቂቃ ከ10 ሴኮንድ አሻሽላዋለች።

በውድድሩ አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ 2 ሠዓት ከ17 ደቂቃ ከ41 ሴኮንድ በመግባት የግል ምርጥ ሰዓቷን በማስመዝገብ ሁለተኛ ወጥታለች።

አትሌት ወርቅነሽ ኢዴሳ 2 ሠዓት ከ21 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ በመግባት ሦስተኛ ሆናለች።

በዱባይ የሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ላለፉት ሰባት ዓመታት በማሸነፍ የበላይነቱን ይዘው እንደነበር ይታወቃል።

በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከ1ኛ እስከ 3ኛ የሚወጡ አትሌቶች በቅደም ተከተል የ100፣ የ40 እና የ20 ሺህ ዶላር ሽልማት ያገኛሉ።

ከ4ኛ እስከ 10ኛ ደረጃ የያዙ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን በአጠቃላይ ለሽልማቱ 385 ሺህ ዶላር ተዘጋጅቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም