የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የሰብል ምርታማነትንና የእንስሳት መኖ አቅርቦትን አሳድጎልናል---የደሴ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች

53

ደሴ ጥር 17/2011 የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የሰብል ምርታማነትና የእንስሳት መኖ አቅርቦትን እንዳሳደገላቸው የደሴ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የደቡብ ወሎ ዞን የተፋሰስ ልማት ሥራ በደሴ ዙሪያ ወረዳ ቀበሌ 37 በሚገኘው ወንቱድማ ተፋሰስ ላይ ተጀምሯል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የደሴ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች እንደተናገሩት በአካባቢው የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የሰብል ምርታማነትንና የእንስሳት መኖ አቅርቦታቸውን አሳድጎላቸዋል።

በደሴ ዙሪያ ወረዳ ቀበሌ 37 የሚኖሩት አርሶ አደር ሸህ ሰይድ አበባው እንዳሉት በየዓመቱ በሚሰራው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው እየተሳተፉ ነው።

"ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በማሳቸውና ተራራማ ቦታዎች ላይ የተሰራው የእርከንና ክትር ሥራ ውጤታማ በመሆኑ ተጠቃሚ ሆነናል" ሲሉም ተናግረዋል።

በለሙ ተፋሰሶች ለእንስሳት መኖ የሚሆኑ የቅንጠባ መኖ ችግኝን ጨምሮ የተለያዩ የሳር ዝርያዎችን በመትከልና በመዝራት ለከብቶቻቸው በቂ መኖ ማግኘታቸውን አስረድተዋል።

በተሰራው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የመሬታቸው የአፈር ለምነት በመጠበቁ በሄክታር ከ15 ኩንታል በታች ከሚያገኙበት ማሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከ25 ኩንታል በላይ ምርት እያገኙበት መሆኑን አመልክተዋል።

በደሴ ዙሪያ ወረዳ የቀበሌ 10 ነዋሪ ወጣት አርሶ አደር ሰይድ ይመር በበኩሉ በአካባቢው ቀደም ሲል በተሰራው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግሯል።

የአፈሩ ለምነት በመጠበቁም 14 ኩንታል ገብስ ከሚያገኝበት ማሳ እስከ 25 ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን አመልክቷል፡፡

"በተከናወኑ የእርከንና ክትር ሥራዎች በሚገድበው የደለል አፈር ላይ ድንች አምርቼ በመሸጥ በዓመት እስከ 10 ሺህ ብር ገቢ እያገኘሁ ነው" ብሏል፡፡

የደሴ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ይመር አርሶ አደሩ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የሚገኘውን ጥቅም በተጨባጭ በማየቱ በልማቱ ለመሳተፍ ያለው ተነሳሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ዘንድሮም በወረዳው 41 ሺህ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በ60 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ በበኩላቸው ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በ2 ሺህ 300 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል፡፡

በተሰራው የተፋሰስ ሥራ የአርሶ አደሩ ምርታማነት ከማደጉ በላይ ለእንስሳት መኖ በቀላሉ ማግኘት እንደተቻለ አመልክተዋል። 

"በህብረተሰቡ ተሳትፎ  አንድ ሺህ 582 ተፋሰሶች ከአንስሳት ንክኪ ነጻ ሆነዋል" ያሉት አቶ ታደሰ፣  ልማቱን ለማጠናከር በባለሙያ የታገዘ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዘንድሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ በተመረጡ አንድ ሺህ 98 ተፋሰሶች ላይ በሚገኝ 521 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

ከወሎ ዩኒቨርሲቲና ከደሴ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመቀናጀት የተሻሻሉ የመኖና የችግኝ ዝርያዎችን በማላመድ ህብረተሰቡን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ 67 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ አጠናና መኖ ተከላ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

በዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ 650 ሺህ አርሶ አደሮች ለማሳተፍ የታቀደ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይም 2 ሺህ አርሶ አደሮች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም