አዴፓ ከለዘብተኝነትና ከይሉኝታ ፖለቲካ ወጥቶ ለህግ መከበርና ለሰላም እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

75

ባህር ዳር ጥር 17/2011 የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከለዘብተኝነትና ከይሉኝታፖለቲካ ወጥቶ ህግን በማስከበርና ሰላምን በማረጋገጥ ሀገራዊ ለውጡ ከግብ ለማድረስ አልሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀ።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ከጥር 13 እስከ 15/2011 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ያካሄደው መደበኛ ጉባኤ ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።

አዴፓ በአቋም መግለጫው እንዳስታወቀው ፓርቲው የህዝቡን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስከበር እንዲሁም የተረጋጋና ለልማት የተመቸ አካባቢን ለመፍጠር አልሞ እየሰራ ይገኛል።

መግለጫው እንዳለው እንደ ሀገርም ሆነ እንደክልል የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ስር እንዳይሰድና ቀጣይነቱ እንዳይረጋገጥ ለማድረግ ፀረ-ለውጥ ቡድኖችና ግለሰቦች አቅማቸውን አሟጠው እየተጠቀሙ ነው፡፡

ክልሉን ከለውጥ ጎዳና በማስወጣት የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል በማድረግ ትርምስ መፍጠር ቀዳሚው አጀንዳ ተደርጎ መወሰዱንም ማዕከላዊ ኮሚቴው መገምገሙን አስታውቋል።

ፀረ-ለውጥ ኃይሎች ባለፉት ዓመታት የነበሩ ስህተቶችንና ይቅርታ የተጠየቀባቸውን ጉዳዮች ሁሉ እንደ አዲስ የማራገብ ስልት እየተጠቀሙ መሆኑንም አስታውቋል።

በእዚህም የክልሉ ህዝብ በድርጅቱ ላይ ያሳደረውን ተስፋ በመሸርሸር ጥላቻ እንዲፈጠር የማድረግ ግብ ይዘው እየሰሩ መሆኑ በማዕከላዊ ኮሚቴው ታምኖበታል።

"ክልሉ በትንንሽ አጀንዳዎች በመጠመድ ህዝቡ ወደ ልማት ሥራ እንዳይገባ በማድረግና መንግስትም ሁሌ በጸጥታ ሥራ ላይ ብቻ እንዲወሰን አቅጣጫ በማሳት በህዝቡ ዘንድ ጥርጣሬ እንዲፈጠርና አለመተማመን እንዲነግስ ጥረት እየተደረገ ነው" ሲልም መግለጫው አመልክቷል።

ህዝብን ከህዝብ በማጋጨትና ሰላምን በማሳጣት የክልሉ ሁለንተናዊ ልማት ወደ ኋላ እንዲጎተትና ሀገራዊ ለውጡ እንዲቀለበስ የሚደረገውን የፀረ ለውጥ አራማጆች አጀንዳ ከዚህ በኋላ በትዕግስት ማለፍ እንደማይቻል ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል።

አዴፓ ከዳተኝነት፣ ከለዘብተኝነትና ከይሉኝታ ፖለቲካ እንዲሁም ከልክ ያለፈ ትዕግስት ወጥቶ ህግን በማስከበርና ሰላምን በማረጋገጥ ለውጡን ለማሳካትና የህዝብ እርካታ ለመፍጠር ግብ ይዞ እየሰራ ነው ብሏል።

በመሆኑም መላው የክልሉ ህዝብ በተለይ ወጣቱ የጀመረውን ህግ የማስከበር ተግባር ከማጠናከር ባለፈ ከአመራሩና ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን በመሰለፍ ለውጡን ከማንኛውም ጥቃት እንዲከላከል ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪውን አቅርቧል።

በምዕራብ ጎንደርና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች የተፈጠረውን የዜጎችን ሞት፣ ንብረት መውደምና ከቀያቸው መፈናቀል ከልብ ማዘኑንም ማዕከላዊ ኮሚቴው አስታውቋል።

ለችግሩ መነሻ የሆነው የሱር ኮንስትራክሽን ድርጅትና በዜጎች ላይ ያልተገባ እርምጃ በወሰዱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ የተጀመረውን የማጣራት ሥራ በፍጥነት በማጠናቀቅ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ በማዕከላዊ ኮሚቴው መወሰኑንም አብራርቷል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ተረጋግተው ኑሯቸውን እንዲመሩ፣ በደረሰው ጉዳት የተፈናቀሉ እንዲቋቋሙ እንዲሁም ለችግር የተጋለጡትን ለመደገፍ በቁርጠኝነት ለመስራት ውሳኔ ላይ ተደርሷል።

በክልሉ የወሰንና የማንነት ጉዳይም "ሌሎች ይሰሩታል፣ በህገ-መንግስቱ ይፈታል" ከሚሉ ለዘብተኛ አቋሞች ፓርቲው በመውጣት በትኩረትና የአካባቢውን ታሪካዊ ዳራ ጭምር ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ ጥያቄው እንዲፈታ ቀጣይነት ያለው ትግልና ክትትል እንደሚደረግም ማዕከላዊ ኮሚቴው በአቋም መግለጫው አስታውቋል።

እየተባባሰ የመጣውን የወጣቶች የሥራ እጥነት ችግር እውቀትን፣ ገንዘብና ጉልበትን በላቀ ሁኔታ በማጣመር ወጣቶችን ከድህነት ለማላቀቅ ርብርብ መካሄድ እንዳለበት ማዕከላዊ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

አዴፓ የክልሉን ህዝብ ሃብት ያለምህረት ሲመዘብሩ በቆዩ አካላት ላይ በሰከነና በበሰለ መንገድ እንዲሁም ማስረጃዎችን መሰረት አድርጎ የጀመረውን የፀረ-ሙስና ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክቷል።

እንደመግለጫው ከሆነ እርምጃው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ባደረሱ አካላት ላይ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በድርጊቱ ተሳታፊና ተባባሪ የነበሩ ቡድኖችና ግለሰቦችም በተመሳሳይ ለህግ እንዲቀርቡ ይደረጋል።

ለእዚህም ድርጅቱ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማዕከላዊ ኮሚቴው ባወጣው የአቋም መግለጫ አረጋግጧል።

መላው የክልሉ ህዝብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ባለሃብቶች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራትና አክቲቪስቶች ወቅቱ የሽግግር መሆኑን ተረድተው በጥንቃቄ፣ በመቻቻልና በመተባበር አግባብ ከፓርቲው ጎን በመሰለፍ የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡም አዴፓ አሳስባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም