ለዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ በነገሌ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ

55

ነገሌ ጥር 16/2011 የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በመምከርና በማስተማር የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ በጉጂ ዞን ነገሌ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡

የሰላም ምክክር መድረክ  ዛሬ በነገሌ ከተማ  ተካሂዷል ።

የከተማው ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ አቶ አብዲ ሮባ  በምክክሩ መድረክ  በሰጡት አስተያየት በየአካባቢው መቻቻልና መከባበር ካልተፈጠረ በጥላቻና ፍረጃ ብቻ የሚገኝ ሰላም እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

"የሰላምን ጥቅምና አስፈላጊነት በማስረዳትና በማስተማር ችግሮች በውይይት  ብቻ እንዲፈቱ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የኃይማኖት አባቶች ተባብረን እየሰራን ነው" ብለዋል፡፡

አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱና የህግ የበላይነት እንዲከበር በጉጂ ኦሮሞ አባገዳዎች የተደረገውን የሰላም ጥሪ ልንጠቀምበት  ይገባል ሲሉም መልክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡

በጉጂ ዞን አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላም ይበልጥ እንዲሻሻል የማስተማርና የመጠበቅ ስራ የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባም  አመልክተዋል፡፡

ከጥላቻ ፣ አንዱ ሌላውን ከመግደልና ከማሳደድ የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ የገለፁት ደግሞ ሌላው የሀገር ሽማግሌ  አቶ መሀመድ አልዬ ናቸው ፡፡

" በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች በአብሮነት ፣ በመከባበርና በመቻቻል ለዓመታት የዘለቀውን  የጥንቱ ባህላችን ተጠናከሮ እንዲቀጥል ሁላችንም ትኩረት ሰጥተን ልንረባረብ ይገባል" ብለዋል ።

አባገዳዎች ፣ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለአዲሱ ትውልድ ባህላዊ የግጭት አፈታት ህግጋቶችን መሰረት በማድረግ የማስተማርና የመምከር   ግዴታቸውን መወጣት እንደሚገባም መክረዋል።

" ሀገርና ሰላምን የመንከባከብና የመጠበቅ ጉዳይ ለመንግስትና ለፖለቲካ ፓርቲ ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁላችንም ተሳትፎ ጥረትና መተባበር የሚጠይቅ ነው " ብለዋል፡፡

ፍርሀትና መሸማቀቅ ቀርቶ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖርና የህግ የባላይነት እንዲከበር መንግስትና ፖሊስም ህጋዊ ስራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አቶ አሬሮ ጃርሶ በሰጡት አስተያየት ትውልዱ ታሪክ አንብቦ በመረዳትና የቀደሙ አባቶቹን ጠይቆ በመረዳት በሀገሩ ተሳስቦ ፣ተረዳድቶና ተፈቃቅሮ እንዲኖር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

" በሀገራችን ታሪክ ርስ በርስ የነበረው ፍቅርና መቻቻል እንዲመለስ ኃላፊነት ወስደን በማስተማርና በማስረዳት በአንዳንድ አካባቢዎች የጠፋው ሰላም እንዲመለስ እንሰራለን" ብለዋል፡፡

የነገሌ ከተማ አስተዳደር  ከንቲባ አቶ ባሊ በዱ የህግ የበላይነትን ማስከበር በአብዛኛው የመንግስት ድርሻ ቢሆንም ያለ ህዝብ ተሳትፎ ሊሳካ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

የአካባቢው ህዝብ ከመንግስት ጎን በመቆም የሰላም ጠንቅ የሆኑት  በማጋለጥና አሳልፎ በመስጠት የድርሻውን እንዲወጣም  ጠይቀዋል፡፡

መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም