በኢትዮጵያ በኤሌክትሮኒክስ የተደገፈ ወረቀት አልባ የህክምና ና የጤና መረጃ ሥርዓት ሊተገበር ነው

129

መቀሌ ጥር16/2011 በኢትዮጵያ  በኤሌክትሮኒክስ የተደገፈ ወረቀት አልባ የህክምና ና የጤና መረጃ ሥርዓት ሊተገበር  ነው፡፡

ሚኒስቴሩ የዲጂታይላይዜሽን የጤና አገልግሎት ሥርዓትን ያስተዋወቀበትን መርሐ ግብር ዛሬ  በመቀሌ አካሂዷል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ  ዳይሬክተር አቶ ኢዮብ ከበደ ለኢዜአ እንዳሉት ሥርዓቱ በሙከራ ደረጃ በትግራይ፣ በአማራ፣በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ተጀምሯል፡፡

በዚህም 1ሺህ60 የጤና ተቋማት እየተተገበረ ነው ብለዋል፡፡

በጤና ተቋማቱ የሚሰሩ 2ሺህ 120 ጤና ባለሙያዎች የኮምፒዩተርና የታብሌት ሞባይል አገልገሎት አሰጣጥ ሰልጥ ነው ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

ሥርዓቱ በጤና ኬላ ደረጃ  እንደሚካሄድና ይህም የሆነበት ዋነኛው ምክንያት የምዝገባና፣ምርመራና የሪፈራል ሥርዓቱ ስለሚጀምር መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ሥርዓቱ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በ34 ሺህ ጤና ኬላዎች በታብሌት ሞባይል ታግዞ ሥራ ላይ ይውላል ብለዋል፡፡

ሥርዓቱን ለማስጀመር ለመሣሪያዎች መግዣ፣ ለሶፍት ዌር መተግበሪያና ለባለሙያዎች ስልጠና ከ210 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም 64 ሺህ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የስድስት ቀናት ስልጠና እንደሚወስዱ አቶ ኢዮብ ገልጸዋል።

ከምዝገባ እስከ ምርመራ፣ከህክምና እስከ ሪፈራል ሥርዓት ያለው ሂደት የተቀላጠፈና ውጤታማ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል፡፡

ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ የክልሎች  የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮዎችና ኤጀንሲዎች ጤና ተቋማት ከሚኒስቴሩ ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በሚኒስቴሩ በተደረገላቸው ድጋፍ ተጠቅመው በ250 ጤና ኬላዎች ላይ ሥርዓቱን በሙከራ ደረጃ  መጀመራቸውን የተናገሩት ደግሞ የትግራይ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሀጎስ ጎደፋይ ናቸው፡፡

በክልሉ በሁለት ዓመታት ውስጥ 17 ሺህ ጤና ኬላዎች በሥርዓቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂው አዲስ በመሆኑ በወረቀትና በታብሌት ሞባይል በሁለቱም እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ ስልጠና ከወሰዱ የጤና ባለሙያዎች መካከል በማዕከላዊ ዞን ወርዒ ለኸ ወረዳ ማይቅነጣል ጤና ኬላ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ሲሰተር ዕቁባ ግደይ ናቸው፡፡

በክልሉ ሀውዜን ወረዳ የመጋብ ጤና ኬላ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ሲስተር መብርሂት ገብረስላሴ በበኩላቸው  በሥርዓቱ በመታገዝ ደንበኛውን በመመዝገብ 8327 ተብሎ በሚታወቀውን የመረጀ ቋት መጠቀም መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱ አሁንም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዳያደርጉት ግን የኔት ወርክ መቆራረጥ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም