ከመከራ በፊት መመካከር !

75

በሰለሞን ደሳለኝ (ኢዜአ-ማይጨው)

አርሶ አደር ጥጋቡ ካሳ በራያ አዘቦ ወረዳ የሐውልቲ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው ፡፡ የስድስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ  ሲሆኑ ዋነኛ መተዳደሪያቸው የእርሻ ስራ ነው ፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የላቸውም፡፡

አርሶ አደር ጥጋቡ በእርሻ ስራ ታታሪ ተብለው ከሚታወቁ የአካባቢው አርሶአደሮች መካከል አንዱ ናቸው ፡፡ እንደ ሌሎች የራያ ገበሬዎች ሁሉ ለአርሶ አደር ጥጋቡም የክረምቱ ዝናብ ሲቀና ጥጋብ የክረምቱ ዝናብ ሲጠፋ ደግሞ የሚበላ ማጣት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡

አንዳንዴ በለስ ይቀና የለ ? ያለፈው አመት የመኸር አዝመራም  ለአርሶ አደር ጥጋቡ የጥጋብ አዝመራ ነበር  ፡፡  90 ኩንታል ማሽላና 40 ኩንታል ጤፍ በማምረትም ስኬታማነታቸውን አሳይተዋል ።

አዝመራውን  ድል የነሱት አርሶአደር ጥጋቡ ጎተራ የሞላውን ምርት ልበ ሙሉ አደረጋቸውና  የደረሰች ሴት ልጃቸውን ለመዳር ተነሳሱ ። የሰርግ ድግስ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ አላጡትም ። ግን  "በቃ ! ፈጣሪ ያውቃል አልኩኝና ለሰርግ ተዘጋጀሁ ” ይላሉ ። መቼ ድግሱ ብቻ ? በአካባቢው ባህል መሰረት እኮ ጥሎሽ የሚሰጠው የሴት ወገን ነው ።

ድግሱም ቢሆን ወገብ የሚቆርጥ ነው ። እንጀራ ፣ መጠጥ ፣ የእርድ ሰንጋዎች ያስፈልጋል  ። እናም በስንት ጥረት የተገኘውን የአዝመራው  በረከት ወደ ገበያ ማውጣት ግድ ይላል ።

” እናም የማሽላ ምርቴን በመሸጥ   ሁለት የእርድ በሬዎች ገዛሁ ፡፡ 25 በርሜል ጠላ ተጠመቀ ፡፡ የጤፍ ምርቱም ለድግሱ እንጀራ ዋለና ቤቴ ባዶውን ቀረ ” ሲሉ በቁጭት ያስታውሳሉ ።

አርሶአደር ጥጋቡ ይህንኑ የግል ገመናቸው በአደባባይ የመሰከሩት በቅርቡ የሰብል ምርት ብክነትን ለመከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ለመምከር የትግራይ ደቡባዊ ዞን መስተዳደር በራያ አዘቦ ወረዳ መሆኒ ከተማ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ነው፡፡

አርሶአደሩ የቆጫቸው ከመጠን በላይ መደገሱ ብቻ አልነበረም የተዘጋጀውም ቢሆን ሳይበላና ሳይጠጣ በመባከኑ እንጂ ። በአካባቢው በጥር ወር የሰርግ ድግስ ይበዛል ። ”ታዲያ ! የአገሬው ሰው ስንቱ ድግስ በልቶ ይዘልቀዋል? ፡፡  እዚህም እዚያም ቀማምሶ ይወጣል ፡፡ የእኔው ድግስ  ዕጣ ፈንታም  ይህንኑ  ሆነና በልቶ የሚጨርሰው ጠፋ ። በቃ! ለጥፋት የተደገሰ  ነበር ” ይላሉ ፡፡

የአካባቢው ሞቃታማ መሆን ደግሞ የጥፋት መጠኑን አባባሰው ። የተዘጋጀው ምግብና መጠጥ ተሎ ለብልሽት አጋለጠው ። ምንም አማራጭ አልነበረኝም፡፡ ለሰርጉ ያለ ቅጥ በገፍ ያሰናዳሁት ወጥና እንጀራ በማግስቱ ቦክቶና ሻግቶ ወደ ቆሻሻ ጣልኩት፡፡ በበርሜሎች የተጠመቀው ጠላም የእንስሳት ሲሳይ ሆነ በማለት ገጠመኛቸውን ለሌሎች አጋሩ ።

እርግጥ በልጄ ጎጆ መውጣት ደስተኛ ነኝ፡፡ ይህን ደስታ ለማግኘት የሰርግ ድግሱን በመጠኑ ማድረግ እችል ነበር፡፡ አላሰብኩበትምና አልሆነም ፡፡ አንድ የአዝመራ ወቅት ሙሉ የለፋሁበትን ምርት በአንድ ጀንበር አወደምኩት ሲሉም ቁጭታቸው ገልፀዋል ።

"የፈሰሰ አይታፈስ"  ከሌሎች ለመፎካከር ብየ ያዘጋጀሁት አቅሜን ያላገናዘበ ድግስ ጉድ ሰራኝ ። ቤተሰቦቼንም ቀለብ አንሶአቸው ወራቶችን በችግር እንዲያሳልፉ አደረግኩኝ አሉና በህዝብ ፊት ቀርቦ መናገሩ በራሱ ያሳፍራል በማለት ሃሳባቸውን ቋጩ ።

የኦፍላ ወረዳ ነዋሪ የአርሶ አደር መጋቢ ስርዓት ሓጎስ ሊቀብርሃን ልምድ ደግሞ ይህንኑ ይመስላል ።  ” ባለፈው አመት ጥሩ ምርት አምርቼ ነበር፡፡ ለክፉ ጊዜ ይጠቅማል ብየ  የቆጠብኩት እህል ግን የለም ” ይላሉ ።

”ሌላው እንደሚያደርገው ሁሉ እኔም ልጄን ለመዳር ተነሳሁ ፡፡ካመረትኩት ምርት የሚሸጠውን ሽጨ ሁለት የአርድ  በሬዎችን ገዛሁ፡፡ ለሰርጉ የተጋገረው የእንጀራ ብዛትም ልክ አልነበረውም ፡፡ 12 በርሜል ጠላም አዘጋጀሁ” ሲሉ ተናገሩ ፡፡

በመጋቢ ስርዓት ሓጎስ ቤት ቅልጥ ያለ ድግስ ተደገሰ ፡፡ ታደሚው የቻለውን ያህል በልቶና ጠጥቶ ቢሄድም ያገኙት ትርፍ ግን አልነበረም ፡፡ ይህን ሲባል ደግሞ የሰርጉ ቀን ካለፈ በኋላ 40 ለሚሆኑ የልጃቸው ሚዜዎች ያወጡትን ወጪ አይጨምርም ፡፡

በአካባቢው ባህል መሰረት በሙሽሮች የጫጉላ ወቅት ሚዜዎች ጨምሮ ለተወሰነ ጊዜ አንድ ላይ መመገብ የመጋቢ ስርዓት ሓጎስ ግዴታ ነበር፡፡ለዚህም እንደገና አንድ ወይፈን ማረድ ያስፈልግ ነበርና አደረጉት ፡፡ በቤታቸው ውስጥም ሙሽራው ልጃቸው ከ40 ሚዜዎቹ ጋር አስቀምጠው ለአንድ ወር ያክል መቀለባቸውን ነው ያስረዱት፡፡

የጫጉላ ጊዜውን ካጠናቀቀ በኋላ በድንገት ልጃቸው ይታመማል፡፡ልጃቸውን ሲታመም መጥተው እግዚአብሄር ይማርህ ያሉት ግን አንድ ወር ከተቀለቡት 40 ሚዜዎቹ መካከል ሶስት ብቻ ነበሩ ፡፡ ሚዜዎቹ የታመመ ጓደኛቸውን ሳይጠይቁ በመቅረታቸው ማዘናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

ልጃቸውን  መዳር ተገቢ ቢሆንም በተንዛዛ ድግስ ምክንያት የደረሰባቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ግን አሁንም ድረስ ያንገበግባቸዋል ። ለአንድ ቀን ደስታ ሲባል ቤተሰቦቼን ለረሃብ ማጋለጥ አልነበረብኝም በማለትም እራሳቸውን ይወቅሳሉ ። እኔን ያየህ ተቀጣ ሲሉም ልምዳቸውን አካፍለዋል ።

 አሁንም ግን በራያ አካባቢ ለሰርግና ምላሽ፡ ለተስካር፡ ለክርስትናና ለሌሎች  ድግሶች የሚሰጠው ግምት ከፍተኛ ነው ፡፡ የባሰው ግን ከሞተ ረጅም አመት ያደረገ ሰውን ለመዘከር ሲባል  ለተስካር ድግስ የሚባክነው ሃብት ልክ ያጣ መሆኑ ነው ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሳይሰሩ ገንዘብ የሚያስገኙ የልመና ድግሶች እየተለመዱ መጥተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች የምረቃ ድግስ በስፋት ይታያል ። 20 አመት ያገለገለ ወፍጮ ሳይቀር መርቁልኝ ብሎ የደገሰ ሰው እንዳጋጠማቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል ።

በሰበብ አስባቡ ህዝቡ ነጋ ጠባ መበዝበዝ የለበትም ሲሉም ድርጊቱን አውግዘውታል ።

በመድረኩ ላይ  በወረዳው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተዘጋጀ አንድ ጥናታዊ ጽሁፍ ለውይይት ቀርቦ ነበር፡፡ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት ደግሞ የፅህፈት ቤቱ ሓላፊ አቶ ሐየሎም ረዳኢ ናቸው ።

በወረዳው የሚገኙ አባወሯ አርሶአደሮች በዓመት በአማካይ ከቀለብ የሚተርፍ 5 ኩንታል እህል ያመርታሉ ። ይህ ትርፍ እህል ግን ለክፉ ቀን ተብሎ የሚቆጠብ አይደለም ። በሰበብ አስባቡ ለድግስ እየተባለ እንደሚባክን ጥናቱ ይጠቁማል  ።

በወረዳው በየአመቱ የሚመረተውን የሰብል ምርት ማባከኛ መንገዶችም በአካባቢው ህዝብ ለረጅም ጊዜ  እየተለመደ የመጣውን ከመጠን ያለፈ የሰርግድግስ ፤ ጥሎሽ፤ የጎጆ መውጪያ ዕቁብ፤ የቤት ምረቃ፤ የተስካር፤ የሰደቃና ክርስትና ድግሶች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ።

በወረዳው በአመት በአማካይ ከ3 ሺህ 400 በላይ የሰርግ ድግሶች ይከናወናሉ ያሉት አቶ ሓየሎም  ከላይ ለተጠቀሱት የድግስ ዓይነቶች በየአመቱ 517 ሚሊዮን ብር የሚገመት ወጪ እንደሚጠይቁ  በጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ አመላክተዋል ።

ህዝቡ ያመረተውን አህል ከመቆጠብ ይልቅ ድግሶች እያባከነ ከድህነትና ከተረጂነት መውጣት አልቻለም፡፡ እንደያውም የሴፍት-ኔት እርዳታ ይገባኛል በሚል መሳሳብ ለግጭት መንስኤ የሆነበት አጋጣሚ እንደነበርም በጥናቱ ተጠቅሷል ።

ድግሶች ጨርሶ ማስቆም ባይቻልም መቀነስ ግን ይቻላል፡፡ ህዝቡ ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለሚዘጋጁ ድግሶች የሚውል የሃብት መጠን እንዲገደብ ማድረግ ነው፡፡ለዚህም በራያዎች ዘንድ ካሁን በፊት የተሞከረውን የአካባቢ ህዝብ የመተዳደሪያ ደንብ በየቀበሌው ተግባራዊ እንዲሆን በጥናታዊ ጽሁፉ የቀረበ መፍትሔ ነው፡፡

የመተዳደሪያ ደንቡ ህዝቡ ተወያይቶ አምኖበት እንዲያፅድቀው ፣ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና የቀበሌ መስተዳድር አካላት ደንቡን እንዲያስፈፅሙ በጥናቱ የተቀመጡ  የመተግበሪያ እቅጣጫዎች ናቸው፡፡

ሼኽ ሁሴን አደም በውይይቱ የተሳተፉ የእንዳመሆኒ ወረዳ እስልምና ጉዳዮች ቃዲ  ናቸው፡፡እሳቸው እንዳሉት በእስልምና እምነትም ይሁን በሌሎች ሃይማኖቶች ብክነትን የሚደግፍ ሃይማኖታዊ ትዕዛዝ የለም ።

”በሸርዓ ህጋችንም የሃብት ብክነት ስለማይፈቅድ ደንብ አውጥተን መስራት ጀምረናል፡፡ደንቡ የሰርግ ወጪ ከፍተኛው 10 ሺህ ብር ብቻ እንዲሆንና ከሙሽሮች ወላጅ አባት በስተቀር ለቤተ አዝማድ አልባሳት ማቅረብ ይከለክላል፡፡”ብለዋል፡፡

መጋቢ ስርዓት ሓጎስ ሊቀብርሃን በበኩላቸው ”የቤቴክርትያናችን ደንብ ማንም ሰው የሞተ ዘመዱን ፀሎተ ፍትሓት ለማድረግ 1ሺህ 500 ብር ብቻ እንዲከፍል ነበር፡፡ ይህን ደንብ እየተከበረ አይደለም፡፡ ለተስካር ድግስ መደገስ በስፋት እየተለመደ መጥቷል፡፡

ለተስካር ድግስ ቢደገስ እንኳን እንዲበሉት የተፈቀደው ሰርተው መብላት ለማይችሉ ነዳያንና ካህን ብቻ ነበር፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ሌላ ነው፡፡ ተስካር ልክ እንደ ሰርግ መፈንጠዚያ ሆኗል፡፡” ይላሉ

በውይይቱ ማብቂያ ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ሓለፎም  እንዳሉት በአካባቢው ገበሬዎች የሰብል ምርትን በቁጠባ የመጠቀም ልምዳቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ እንጂ የመሻሻል ምልክት እያሳየ  አይደለም።

ብክነቱን ተከትሎ ደግሞ በአካባቢው ከሚኖሩ አርሶአደሮች መካከል ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሴፍት-ኔት እርዳታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምክንያት ሆኗል፡፡

የሃብት ብክነትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባይቻልም መቀነስ ግን ይቻላል የሚል እምነት እንዳላቸው ዋና አስተዳዳሪው ይናገራሉ ፡፡ መፍትሔው ደግሞ በጥናታዊ ፅሁፉ የተጠቆመውን መተግበር ነው ።

አርሶ አደራችን ጥሮ ግሮ የሚያመርተውን ሰብል በተጋነነ ድግስ ምክንያት ባዶ እጁ ሲቀር መመልከት ያማል ። ስለዚህ በዘርፉ የሚታዩ የአመለካከት ግድፈቶችን በማረም የቁጠባ ባህል እንዲያዳብር ማገዝ ደግሞ የሁላቸንም ድርሻ መሆን አለበት ።

ቁጠባ ከራስ ተርፎ ለምጣኔ ሀብታዊ እድገት ፋይዳው የጎላ ነውና በመቆጠብ ክፉ ጊዜን መሻገር ፣ በመቆጠብ ኢኮኖሚያዊ አቅማችንን ማሳደግና በራስ የመተማመን መንፈሳችንን ማጎልበት ይጠበቅብናል የፀሃፊው መልእክት ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም