የመንግስትና ኦነግ ውጊያ እንዲቆምና የኦነግ ሠራዊት ትጥቅ ፈትቶ ወደ ካምፕ እንዲገባ ውሳኔ ተላለፈ

88

አምቦ ጥር 16/2011 አምቦ ላይ በተካሄደው የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና የኦነግና የእርቀ ሠላም ጉባዔ ውጊያ እንዲያቆሙና የኦነግ ሠራዊትም በ20 ቀናት ውስጥ ትጥቅ ፈትቶ ወደ ካምፕ እንዲገባ ውሳኔ ተላለፈ።

በጉባኤው አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሁለቱ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ ምሁራን፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የአምቦና አካባቢው ነዋሪዎችና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ የአመራር አባላት ተሳትፈዋል።

ጥር 14 ቀን 2011 ዓ.ም በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል እርቅ ለማውረድ በአዲስ አበባ በተካሄደው ጉባኤ 71 አባላት ያሉት የቴክኒክ ኮሚቴም ተቋቁሟል።

ይህን ተከትሎ ኮሚቴው ትናንት ባካሄደው ስብሰባ ባለ 6 አንቀጽ የውሳኔ ሐሳቦች ላይ ተወያይቶ ዛሬ ውሳኔ አሳልፏል።

በዋናነት የህብረተሰቡን ሠላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ከዛሬ ጀምሮ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው ጦርነት እንዲቆም ውሳኔ ተላልፏል።

በክልሉ ዘላቂ ሠላም ለማስፈንም የኦነግን ሠራዊት በ20 ቀናት ውስጥ ወደ ካምፕ የማስገባት ስራ እንደሚከናወን ኮሚቴው አሳውቋል።

ወደ ካምፕ ለሚገባው የኦነግ ሠራዊት ደማቅ አቀባበል የሚደረግለት ሲሆን በሁለት ወራት የካምፕ ቆይታው የተለያዩ ስልጠናዎችን ይወስዳል።

ከስልጠናው በኋላ እያንዳንዱ አባል እንደ ፍላጎቱ በግል ስራ መሠማራት ወይም ወደ መንግስት የሠላም ማስከበር ኃይል መቀላቀል እንደሚችልም ተነግሯል።

ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው በዚህ ውሳኔ ላይ ሁለቱ ፓርቲዎች በሚዲያ ትችትና የአቋም መግለጫ መስጠት እንደማይችሉም ተገልጿል።

ይህን ውሳኔ ለመተግበር ፈቃደኛ በማይሆን አካል ላይ ኅብረተሰቡ መረጃ በመስጠት እንዲተባበርና ከኮሚቴውም ጎን እንዲቆም ጥሪ ተላልፏል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም