የክልሉን ህዝብ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ ነው...ዶክተር ደብረጽዮን

67

መቀሌ ጥር 16/2011 የክልሉን ሰላም ከማረጋገጥ ባለፈ ለህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት በትኩረት እየተሰራ  መሆኑን የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በመቀሌ ከተማ ለተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የስድስት ወራት የስራ እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት የክልል መንግስትና ህዝብም ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል።

የክልል መንግስትና ህዝብም ያጋጠሙትን ችግሮች በትእግስት በማሳለፍና የክልሉን ሰላም በማጎልበት በመስራቱ ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመሸጋገር መደላድል መፈጠሩን ተናግረዋል

ከአጎራባች ክልል መንግስታትና ህዝቦች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተው የተጀመረው የኢትዮ-ኤርትራ መልካም ግንኙነትም የሰላም ጉዞውን ውጤታማ እያደረገው መምጣቱን አመላክተዋል።

የክልሉ መንግስት ባለፉት ስድስት ወራት በህዝቡ ሲነሱ የቆዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት በጥናቶች የታገዙ የመፍትሄ እርምጃዎችን መወሰዱን አስረድተዋል።

በፍትህ አሰጣጥ፣በማዘጋጃ ቤቶች አገልግሎት፣በገጠር መሬት አስተዳደርና የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ ችግሮች እንደሚታዩ ተናግረዋል።

ከህዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንደማይሰጥ ያነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ከ20 ዓመታት በላይ የቆየው የክልሉን የአስተዳደር አደረጃጀት ለማሻሻል የሚረዳ አዲስ የአደረጃጀት  ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑንም ተናግረዋል።

አዲሱ አደረጃጀት በቀጣይ ወደ ህዝቡ ወርዶ ውይይት እንደሚደረግበትም አመልክተዋል።

የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር አዋጅ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ወደ ምክር ቤት ቀርቦ እንዲሻር መደረጉን ዶክተር ደብረጺዮን አስታውቀዋል።

የማህበራዊ ፍርድ ቤት የአገልግሎት አሰጣጥ ሌላው የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ እንደሆነ የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ነባሩን አደረጃጀት በማፍረስ  አዲስ አደረጃጀት ለምክር ቤቱ ለውሳኔ መቅረቡን አስረድተዋል።

በቀበሌ ደረጃ አንድ ቋሚ ስራ አስኪያጅ ብቻ የነበረው የአስተዳደር መዋቅር በአዲሱ አደረጃጀት ሶስት ቋሚ የካቢኔ አባላት እንዲኖሩት በክልሉ ስራ አስፈፃሚ መወሰኑን ጠቁመዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ድህነትን ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ በተከናወነው ስራ  የግብርናው ዘርፍ  ለአግሮ ኢንዱስትሪው  እንዲመግብ መደረጉን ጠቁመዋል።

በከተማ ደረጃ ያሉት የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለከተሞች የኢኮኖሚ ሽግግር ካላቸው አስተዋፅኦ አንፃር ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ 90ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

የክልሉን የኢንቨስትመንት አመቺነት ይበልጥ ለማጠናከር ጽህፈት ቤቱ በአዲስ አደረጃጀት እንዲዋቀር ለምክር ቤቱ መቅረቡን የተናገሩት ዶክተር ደብረፅዮን ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ለ867 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን አመልክተዋል።

በተጠናቀቀው ግማሽ የበጀት አመት 2 ነጥብ 5 ቢልዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ድረስ 2 ነጥብ 1 ቢልዮን ብር ሊሰበሰብ መቻሉን አብራርተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በደደቢትና አደዳይ ማይክሮ ፋይናንሶች 583 ሚልዮን ብር ሊቆጠብ መቻሉን ያስረዱት ምክትል ርዕሰ መሰተዳደሩ "ይሄም በህብረተሰቡ ያለው የቁጠባ ባህል አለመዳበሩን የሚያመላክት ነው" ብለዋል።

ከክልሉ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 113 ሚልዮን ዶላር መገኘቱን የተናገሩት ዶክተር ደብረፅዮን ይህም  ከእቅዱ አንፃር ሲታይ አነስተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይም በመዓድን ዘርፍ ያለውን ድክመት ለመፍታት ይበልጥ ሊተኮርበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዛሬ የተጀመረው የክልሉ 5ኛ ዘመን 14ኛ መደበኛ ጉባኤ ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን የተለያዩ አዋጆችና ተጨማሪ በጀትን በማጽደቅ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም