በዱባይ ማራቶን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል

507

አዲስ አበባ ጥር 16/2011 በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ነገ በሚካሄደው የዱባይ ማራቶን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

ባለፈው ዓመት የዱባይ ማራቶን በወንዶች ኢትዮጵያዊው አትሌት ሞስነት ገረመው በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሮዛ ደረጃ የቦታውን ክብረ ወሰን አሻሽለው ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው።

በወንዶች 14 ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አትሌት ጉዬ አዶላ፣ አትሌት አሰፋ መንግስቱ፣ አትሌት ሲሳይ ለማና አትሌት ለሚ ብርሃኑ ውድድሩን ያሸንፋሉ ከተባሉት መካከል እንደሆኑ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ-ገጹ አስፍሯል።

አትሌት ኢብራሂም ጄላንና አትሌት ጌታነህ ሞላ በማራቶን የመጀመሪያ ውድድራቸውን ያደርጋሉ።

ኬንያዊው አትሌት ኢማኑኤል ሳይናና በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ስዊዘርላንዳዊ የሆነው አትሌት ታደሰ አብርሃም የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ዋንኛ ተፎካካሪ መሆናቸው ተገልጿል።

በሴቶች ስምንት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በማራቶን ውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ፣ አትሌት ረሂማ ቱሳና አትሌት ሱሌ ኡቱራ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ ትዕግስት አሰፋ በማራቶን የመጀመሪያ ውድድሯን ታደርጋለች።

ኬንያውያኖቹ አትሌቶች ሩት ቼፕጌቲችና ሻሮን ቼሮፕ የኢትዮጵያዊያኖቹ አትሌቶች ዋንኛ ተፎካካሪ መሆናቸውን የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በዘገባው አመልክቷል።

በነገው ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡ አትሌቶች በቅደም ተከተል የ100፣ 40 እና 20 ሺህ ዶላር ሽልማት እንደሚያገኙ የውድድሩ አዘጋጆች ገልጸዋል።

በውድድሩ ከአራት እስከ 10 የሚወጡት አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን አጠቃላይ 385 ሺህ ዶላር ሽልማት ለአትሌቶች ተዘጋጅቷል።

ባለፈው ዓመት ውድድር በአጠቃላይ 816 ሺህ ዶላር ሽልማት የተበረከተ ሲሆን የዘንድሮ ሽልማት ካለፈው ዓመት አንጻር በ431 ሺህ ዶላር ቀንሷል።

“የዓለም ውዱ ማራቶን” የሚል ስያሜ የነበረው የዱባይ ማራቶን የሽልማት መጠኑ መቀነሱን ተከትሎ ከዚህ በኋላ “የዓለም ውዱ ማራቶን” መሆኑ እንዳበቃ ተገልጿል።

ለ20ኛ ጊዜ የሚካሄደው የዱባይ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።

ባለፈው ዓመት የዱባይ ማራቶን ውድድር በወንዶች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከአንድ እስከ 10፤ በሴቶች ከአንድ እስከ ሰባት በመውጣት በበላይነት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2000 የተጀመረው የዱባይ ማራቶን እስካሁን 19 ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሴቶች 14 ጊዜ በወንዶች ደግሞ 12 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነትን ይዘዋል።