በባሌ በመኽር ወቅት የለማው የቅመማ ቅመም ምርት እየተሰበሰበ ነው

352

ጎባ ጥር 15/2011 በባሌ ዞን በመኸሩ ወቅት 16 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማው የቅመማ ቅመም ምርት የመሰብሰብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ ።

ቅመማ ቅመሙ የለማው በዞኑ 12 ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡

የዞኑ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ በሽር በከር ለኢዜአ አንደገለጹት ከለማው  ቅመማ ቅመም ውስጥ ጥቁርና ነጭ አዝሙድ፣ ድምብላል፤ በርበሬና  አብሽ ይገኙበታል፡፡

በልማቱ በመሳተፍ ላይ ካሉት 13 ሺህ አርሶ አደሮች መካከል 1 ሺህ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆን  እየተሰበሰበ ካለውም ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ የቅመማ ቅመም ምርት እንደሚገኝ  በቅድመ ምርት ግምገማ ተገምቷል ።

“በዞኑ በልማቱ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከሚያደርጉት ጥረት በተጓዳኝ  ገበያ ተኮር በሆኑ ሰብሎች ላይ በመሳተፍ  በዓመት ሁለት ጊዜ እያለሙ ናቸው “ብለዋል፡፡

አርሶ አደሩ ከገበያ ጋር ተያይዞ የሚያነሳውን ቅሬታ ለመፍታት በምርቱ ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ የሚያቀርቡ ህብረት ሥራ ማህበራት፣ ባለሀብቶችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል ።

ኃላፊው እንዳሉት በቀጣይ አርሶ አደሩ በተደራጀ መልኩ በሚያመርተው የቅመማ ቅመም ምርት ላይ እሴት በመጨመር እስከ ውጭ ገበያ  በመላክ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን  በመንግስት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በጎሮ ወረዳ የወልተኢ አማና ቀበሌ አርሶ አደር አብዱ ሼይሞ በሰጡት አስተያየት  በመኽሩ ወቅት በሁለት ሄክታር መሬታቸው ላይ ካለሙት ጥቁር አዝሙድ ጥሩ ምርት እንደሚያገኙ የሚጠብቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተለያዩ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም ምርታማነትን በእጥፍ በማሳደግ በሄክታር እስከ 20 ኩንታል ምርት  መሰብሰብ ቢችሉም የገበያ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዋዥቀ እንዳስቸገራቸው ተናግረዋል ፡፡

ከዚህ በፊት በአካባቢያቸው ገበያ ኪሎውን  ግራም ጥቁር አዝሙድ እስከ 60 ብር መሸጣቸውን ያስታወሱት አርሶ አደሩ በአሁኑ ወቅት ወርዶ በ18 ብር ሂሳብ እየተሸጠ እንደሚገኝ በማሳየነት አቅርበዋል፡፡

ሌላው የልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደር አብዱልቃድር ሰኢድ በበኩላቸው  በቅመማ ቅመም ልማት የመሳተፍ የቆየ ልምድ ቢኖራቸውም የገበያ አማራጫቸው በአካባቢያቸው ብቻ የተደገበ በመሆኑ የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡

” እኛ በብዙ ልፋት የምናመርተውን በአካባቢው ነጋዴዎችና ደላሎች እየተነጠቅን ስለሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ይበልጥ ተጠቃሚ እንድንሆን የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩልን እንፈልጋለን ” ብለዋል፡፡

የቅመማ ቅመም ምርት በገበያ ላይ ተፈላጊ እንደሆነ ቢያውቁም የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የጎሮ አካባቢ ቀበሌው አርሶ አደር መህሙድ ከድር ናቸው ፡፡

በአሁኑ የመኽር ወቅትም ከአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት በኩታ ገጠም ማሳቸው ላይ ጥቁር አዝሙድ በማልማት ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት አርሶ አደሩ ” መንግስት  ከልማቱ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድንሆን የገበያ ትስስር ሊፈጥርልን ይገባል” ብለዋል፡፡