ለሰላም መከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢ ነዋሪዎች ገለጹ

346

ነቀምት ጥር 15/2011 ለአካባቢያቸው ሰላም መከበር ተቀራርበው በመስራት የድርሻቸውን እንደሚወጡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስታት የጋራ የሠላምና የልማት ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ያዘጋጀው የእርቀ ሰላም መድረክ በስኬት ተጠናቋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች መካከል ከአራት ወር በፊት ተከስቶ የነበረው ግጭት ለበርካታ ሰዎች ህልፈትና ንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑ ይታወቃል ።

ችግሩን በዘላቂነትለመፍታትና ቀጣይነት ያለው ሰላም ለማረጋገጥ ከምስራቅ ወለጋ 6 ወረዳዎችና ከካማሺ ዞን ሁለት አዋሳኝ ወረዳዎች የተውጣጡ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የወረዳ፣ የዞን፣ የክልል አመራሮችና የመከላከያ ሠራዊት ኃላፊዎች በተገኙበት የእርቀ ሰላም መድረክ ትናንት ተካሔዳል።

በምስራቅ ወለጋ ዞን በሎ ጀገንፎኢ ወረዳ አንዱራ በሎ ቀበሌ በተካሔደው የእርቀ ሰላም መድረክ ላይ ከ400 የሚበልጡ የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

እርቀ ሰላሙ ሲጠናቀቅ ባለስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ ያወጡት የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጣይ ለአካባቢው ሰላም እጅ ለእጅ ተያይዘው በመስራት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የተፈናቀሉትን ወገኖቻቸውን ለመመለስ እንዲሁም ከሥራ ገበታቸው የተፈናቀሉ የመንግስት ሠራተኞች ወደስራቸው ለመመለስ በጋራ እንደሚንቀሳቀሱም ተናግረዋል።

ውይይቱን እስከ ቀበሌ ድረስ በማውረድ የጋራ ትስስራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል።

የካማሺ ዞን በሎ ጀገንፎኢ ወረዳ የአንገር ዋጃ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት በቀለ ደምሴ በሰጠው አስተያየት በተደረገው እርቀ ሰላም መደሰቱን ተናግሮ ለወደፊቱም አብሮነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግሯል፡፡

የሐሮ ሊሙ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አያንቱ ኦላና በበኩላቸው እርቅ መውረዱ እንዳስደሰታቸው ገልጸው በግጭቱ የጠፋባቸውን ንብረት መንግሥት ክትትል አድርጎ እንዲመልስላቸው ጠይቀዋል፡፡

በቀጣይ ለአካባቢያቸው ሰላም መረጋገጥ ትኩረት ሰጥተው በመስራት የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

የካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገርቢ ሎላሣ እርቀ ሠላሙን በማስመልከት እንደተገሩት ግጭቱ የኦሮሞና የጉሙዝ ሕዝቦች የፈጠሩት ሳይሆን በአቋራጭ መክበርን የሚፈልጉ ኪራይ ሰብሳቢዎች የጠነሰሱት ሴራ ነው።

” ሁለቱን ሕዝቦች የሚያለያይ ምንም ነገር የለም ” ያሉት ዋና አስተዳዳሪው እርቀ ሠላሙ ለአራት ወራት ተለያይተው የኖሩ ወንድማማች ህዝቦችን ስለሚያገናኝ ለሁለቱም ሕዝቦች ከፍተኛ ስኬት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በግጭቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በምስራቅ ወለጋ ዞን ተጠልለው የሚገኙ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰው የጠፋባቸውን ንብረቶች እንዲያስመዘግቡ ይደረጋል። 

የክልሉ መንግስትም በአካባቢው ካለው ኮማንድ ፖስት ጋር በመሆን የተዘረፉ ንብረቶችን፣ ከብቶችንና ሌሎች ሀብቶችን የማስመለስና አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ሥራ እንደሚያከናውን ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው የሕግ የበላይነት ተከብሮ የተዘጉ መንገዶችን በመክፈት የገበያና የንግድ እንቅስቃሴ መጀመር እንዳለበትም አቶ ገርቢ አሳስበዋል፡፡

የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ በቀለ በበኩላቸው በሁለቱ ሕዝቦች መካከል መተማመን፣ መከባበር፣ መቻቻል፣ መደጋገፍ እና መደማመጥ ሊኖር እንደሚገባና ግጭቶች ቢፈጠሩ እንኳ በሠላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመፍታት ባህል መዳበር እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ኃላፊ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው ” የተደረሰው እርቀ ሰላም አብሮነታቸውን አጠናክረው ለበርካታ ዓመታት የኖሩትን ሕዝቦች መልሶ ያገናኘ ትልቅ ስኬት ነው” ብለውታል ፡፡

በአካባቢው የሚገኙ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችም የሰላም አምባሳደር በመሆን ሕዝቦቹን የማገናኘት ኃላፊነታቸውን እንዲያጠናክሩ ዶክተር ሀብታሙ አሳስበዋል፡፡