ቀልጣፋና ደህንነቱ የተረጋገጠ የትራንስፖርት አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው

65

አዳማ ጥር 15/2011 ቀልጣፋና ደህንነቱ የተረጋገጠ የትራንስፖርት አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን አስታወቀ።

‘’ለክልልና ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ አመራሮች የስድስት ወር ዕቅድ አፈፃጸምና ቀጣይ እቅድ’’ ላይ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ተጀምሯል።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ፍሰሃ መብርሀቶም እንዳስታወቁት የትራንስፖርት ዘርፉ የጥራት ደረጃውና አስተማማኝነቱ ተጠብቆ ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን እየተሰራ ነው።

በመጀመሪያው ግማሽ የበጀት ዓመት የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሳደግ በተሰራው ስራ ከ268 ሚሊዮን 164 ሺህ ህዝብ በላይ ማጓጓዝ መቻሉን የገለጹት ዳይሬክተሩ ይህም አፈፃጸም ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር በሶስት በመቶ ብልጫ መኖሩን አመልክተዋል።

የገቢ ምርቶችን በኮምቦልቻ፣ በአዋሳና በምስራቅ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የመጫን፣ የማራገፍና የአቅርቦት ክፍተት እንዳይፈጠር ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ ስራ መከናወኑንም ተናግረዋል።

በግማሽ የበጀት ዓመቱ  በገቢና በወጭ ምርቶች 6 ነጠብ 3 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ፣ ስንዴ፣ ስኳር፣ብረት፣ ድንጋይ ከሰልና ሌሎችንም ምርቶች ከወደብ ወደ አገር ውስጥ በጭነት ተሽከርካሪ ለማጓጓዝ ታቅዶ 81 ነጥብ 5 በመቶ መከናወኑን  አስረድተዋል።

በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን የሰው ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ለመከላከል የሌሊት ጉዞ ለመቀነስ የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ የጋራ አቅጣጫ መያዙንም ገልጸዋል።

የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ትምህርት በሀገሪቱ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተትም አንድ የመነሻ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለትምህርት ሚኒስቴር መላኩንም አቶ ፍሰሀ ጠቁመዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የደረሱ የትራፊክ አደጋ መረጃዎችን በማጠናቀር የትራፊክ አደጋ መንስኤዎችና ትስስራቸው የደረሱበትን ደረጃ የሚያሳይ ጥናት መካሄዱንም አመለክተዋል።

የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ለማሻሻል 120 ሺህ ብሮሸሮች ተዘጋጅተው የተሰራጩ ሲሆን ትምህርታዊ የቴሌቭዥም መርሃ ግብር እንዲዘጋጅ መደረጉን ገልጸዋል።

በመንፈቅ ዓመቱ የተሽከርካሪ ብቃት ለማረጋገጥ፣የትራንስፖርት አገልግሎት አደረጃጀትና አሰራር ለማሻሻል፣የአውቶሚቲቭ ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም የህዝብና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና ለማረጋገጥና በሌሎችም መስኮች ሰፊ ሰራ መሰራቱን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

የደቡብ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የእቅድና በጀት ዳይሬክተር አቶ አስራት አይዬ ባለፉት ስድስት ወራት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሳለጥ 80 አዳዲስ የስምሪት መስመሮች መከፈታቸውን ገልጸዋል።

በእዚህም 900 ሺህ ህዝብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው የተናገሩት።

በእዚህ ጊዜ ውስጥ 71 ሺህ 719 ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት ህግና ደንብ ጥሰው በመገኘታቸው ከ18 ሚሊዮን 837 ሺህ ብር በላይ እንዲቀጡ በማድረግ ለመንግስት ገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ በደረሰ የትራፊክ አደጋም በ300 ሰዎች የህይወት መጥፋት፣ 328 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ሲደርስ 11 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረትም ወድሟል። 

ከሙስና ጋር በተያያዘም የተግባር ፈተና ያልወሰዱ 233 ዕጩ አሽከርካሪዎች እንደተፈተኑ ተደርጎ መንጃ ፈቃድ እንዲታተም ጥያቄ ያቀረቡ ሶስት ሰራተኞች ከስራ የማሰናበትና በእስራት እንዲቀጡ መደረጉን አስታውቀዋል።

ለሶስት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ ከሁለቱ መስተዳድርና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን በስድስት ወራት የስራ አፈፃጸም ላይ በመምከር የቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም