ለመላ ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር ስኬታማነት ድጋፍ ይደረጋል-የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

61

መቀሌ ጥር 15/2011 መቀሌ የምታስተናግደው ለሦስተኛው የመላ ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ስፖርት ውድድር ስኬታማነት ድጋፍ እንደሚደረግ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል አረጋገጡ።

ምክትል ርዕሰ መሰተዳድሩ ከመጋቢት 2011 አጋማሽ ጀምሮ በክልሉ ለሚያዘጋጀው ውድድር እየተደረገ ያለውን ዝግጅት ለመገምገም ወደ ከተማዋ ከተጓዘው ከፌደራል ስፖርት ኮሚሽንና ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ልዑካን ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

ዶክተር ደብረፅዮን በወቅቱ እንደገለጹት ውድድሩ ተማሪዎች እርስ በራሳቸው የሚተዋወቁበት፣ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበትና ባህላቸውን የሚለዋወጡበት መድረክ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል።

"ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ  ዝግጅቱ የተሟላ እንዲሆን ድጋፍ ይደረጋል " ሲሉም ተናግረዋል ።

የፌደራል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው በክልሉ ለሚካሄደው ውድድር እየተደረገ ያለው ዝግጅት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል ።

"ዝግጅቱ ኃላፊነት በተሞላበት መንፈስ እየተካሄደ መሆኑን ተገንዘበናል"ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ኮሚሽኑ ከዝግጅቱ የተሻለ ልምድ የሚቀስምበት አጋጣሚ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ያልተጠናቀቁ ሥራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

"የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ጨዋታዎች የሁሉም ስፖርቶች መሰረት ናቸው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ናቸው።

ለዚህም "ውድድሩን ለመደገፍ ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣለን" ብለዋል።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ተወካይ አቶ ኪሮስ ሐዱሽ ውድድሩን ለማሳካት በቂ የመጫወቻ ሜዳዎች፣ መዋኛ ገንዳና አዳራሾች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ።

ስፖርተኞች የሚያርፉባቸው የመኝታ ቦታዎች፣ ምግብ ቤቶች፣ መዝናኛ ሥፍራዎች፣የሕክምና ማዕከላትና የትራንስፖርት አገልግሎት መሰናዳታቸውንም  አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም