ኢትዮጵያውያን ዳኞች በዓለም አቀፍና የአፍሪካ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ እንዲያጫውቱ ተመረጡ

90

አዲስ አበባ  ጥር 15/2011 ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል በቅደም ተከተል ፖርቹጋል እና ኒጀር ላይ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ እንዲዳኙ መመረጣቸውን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ከየካቲት 20 እስከ የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ.ም በፖርቹጋል አስተናጋጅነት የሚካሄደውና 12 ሴት ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበት የአልጋርቬ ዋንጫ ላይ እንድታጫውት የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ መርጧታል።

ሊዲያ በፊፋ አባል አገራት በሚገኙት ስድስቱ አህጉራዊ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽኖች ውስጥ ከተመደቡት ዋና ዳኞች መካከል የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን (ካፍን) ከሚወክሉት ዳኞች መካከል አንዷ መሆኗን እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

በአልጋርቬ ዋንጫ ውድድር በዋና ዳኝነት ዘጠኝ ዋና ዳኞችን ከዘጠኝ አገራት እንዲሁም 18 ረዳት ዳኞችን ከ14 አገራት ተመራጭ ሆነዋል።

በሌላ በኩል በኒጀር አስተናጋጅነት ከጥር 25 እስከ የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው በቶታል ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በረዳት ዳኝነት እንዲመራ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል መመረጡን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን /ካፍ/ በላከው ዝርዝር መግለጹን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

በአገር ውስጥ ሊግ በሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ በሚካሄደው ውድድር ላይ ኢትዮጵያዊው ዳኛ ተመስገንን ጨምሮ በዋና ዳኝነትና ረዳት ዳኝነት በተመሳሳይ 12 ዳኞች ተመርጠዋል።

ከውድድሩ በፊት ለባለሙያዎቹ የአካል ብቃት፣ የንድፈ ሃሳብና የሙያ ምዘና እንደሚደረግላቸው እና በብቃት መወጣት የቻሉ ዳኞች ብቻ ውድድሩን እንደሚመሩም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም