በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመገናኛ ብዙኃን አውደ ርዕይ ሊካሄድ ነው

1246

አዲስ አበባ ጥር 15/2011 በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመገናኛ ብዙኃን አውደ ርዕይ ከጥር 17 እስከ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሊካሄድ ነው።

በ”ኦን ፕሮሞሽን” የተዘጋጀው አውደ ርዕይ በመገናኛ ብዙኃን መካከል የቴክኖሎጂና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር የሚያግዝ ነው።

የአውደ ርዕዩ አስተባባሪ አቶ ቴዎፍሎስ መኮንን ዛሬ በሰጡት መግለጫ የአውደ ርዕዩ ዓላማ በመገናኛ ብዙኃን መካከል ትብብር እንዲኖርና የልምድ ልውውጥ እንዲዳብር ማድረግ ነው።

በአሁኑ ወቅት የመገናኛ ብዙኃን በተናጠል እየሰሩ በመሆኑ አውደ ርዕዩ እያንዳንዱ የመገናኛ ብዙኃን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና አሰራር የሚያውቁበትን ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።  

እንዲህ ዓይነቱ አውደ ርዕይ በሰለጠኑ አገራት እንደሚካሄድ የገለጹት አቶ ቴዎፍሎስ በርካታ ግብዓቶች የሚገኙበት እና የእርስ በርስ ግንኙነት የሚፈጥሩበት መድረክ ሲሆን በኢትዮጵያም ይህን እውን ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በሚካሄደው አውደ ርዕይ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴርና በአዲስ አበባ ዩኒቨሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ጨምሮ 70 የመገናኛ ብዙኃን ተሳታፊ እንደሚሆኑም ገልጸዋል። 

አውደ ርዕዩ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን በቀጣይ የአውሮፓ፣ የመካከለኛው ምስራቅና የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን ተሳታፊ ለማድረግ መታቀዱንም አቶ ቴዎፍሎስ አመልክተዋል።

በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከጥር 17 እስከ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው የመገናኛ ብዙኃን አውደ ርዕይ ለጎብኝዎች ነጻ መሆኑን አስተባባሪው አስታውቋል።