ከ106 ሺህ ዩኒት በላይ ደም መሰብሰቡን የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት አስታወቀ

88

አዲስ አበባ  ጥር 15/2011 በ2011 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ106 ሺህ በላይ ዩኒት ደም በአገር አቀፍ ደረጃ መሰብስቡን የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።

የደም ባንክ አገልግሎቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው፤ በየወቅቱ የሚገጥመውን የደም እጥረት መፍታት የሚያስችሉና በደም ልገሳ ማዕከላትና በደም መለገሻ ተሽከርካሪዎች የታገዘ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።

በኢትዮጵያ የደም ልገሳ ከተጀመረበት ከ1962 ዓ.ም ጀምሮ በሰብዓዊነት የሌሎችን ህይወት ለመታደግ የደም ልገሳን በቋሚነት የሚያደርጉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ደም የማይለግሱ ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ ነው።

በዚህም አሁን ላይ እየተሰጠ ያለው የደም መጠን ከአገልግሎት ፈላጊዎች ቁጥር አንጻር ሲታይ አነስተኛ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ደም መለገስ የሚሹ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ገልጿል።

የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ሄለና ኃይሉ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ጊዜ ወስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ106ሺ ዩኒት በላይ ደም ተሰብስቧል ብለዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ ፤ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ በጥር ወር በመንግስትና በግል ተቋማት የሚገኙ ስራተኞች በፍቃደኝነት የደም ልገሳ እያደረጉ መሆኑንም አስታውሰዋል።

ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ በበጎ ፍቃደኝነት ደም ለመለገስ የሚመጡ ስዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑንም አመላክተዋል።

ህብረተሰቡ ደም በመለገስ የሰዎችን ህይወት እንዲታደግም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም