ኮርፖሬሽኑ ያደረገው ጭማሪ በሌላ ጥናት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የንግድ ቤቶች ተከራዮች ማህበር ጠየቀ

117

አዲስ አበባ ጥር 15/2011 የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በንግድ ቤቶች ላይ ያደረገው የኪራይ ተመን ጭማሪ በአዲስ ጥናት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የንግድ ቤቶች ተከራዮች ማህበር ጠየቀ።

ኮርፖሬሽኑ በቤቶቹ ላይ ጭማሪ ከማድረጉ በፊት ሰፊ ጥናት ማካሄዱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ማህበሩ ኮርፓሬሽኑ ባደረገው የኪራይ ተመን ጭማሪ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህ ጊዜ የማህበሩ ሰብሳቢ ወይዘሮ ስምሀል መኮንን እንደገለጹት፤ የንግዱ ማህበረሰብ ላይ የተደረገው የንግድ ቤቶች የኪራይ ዋጋ ተመን ሁሉንም ወገን በማሳተፍ የተካሄደ ጥናት አይደለም።

በመሆኑም የተደረገውን ጭማሪ ኮርፖሬሽኑ አግዶ በምትኩ ሁሉን ያሳተፈና አከራይና ተከራይን የሚያቀራርብና አዲስ ጥናት እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

ኮፖሬሽኑ የንግድ ቤቶችን በጨረታ፣ በጨረታ መነሻ፣ በኪራይ አከራይ፣ ለሶስተኛ ወገን ሲተላለፍና የቀድሞ መነሻ ዋጋ ኪራይን በሚሉ መርሆች

ቤቶቹን እያስተዳደረ ይገኛል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በበኩሉ ከዚህ በፊት በንግድ ቤቶች ላይ ጭማሪ ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ማብራሪያ መስጠቱ ይታወሳል።

ከንግድ ቤቶች የሚያገኘው ገቢ ከግሉ ዘርፍ ጋር ሲነፃፃር ዝቅተኛ መሆኑ፣ የንግድ ቤቶቹ ዋጋ አነስተኛና ተመኑ ለረጅም ዓመታት የቆየ መሆኑ ተጠቅሷል።

ከኮርፖሬሽኑ ተከራይተው ከፍ ባለ ዋጋ በማከራየት ያለአግባብ የሚጠቀሙና የቤቶቹን ቁልፍ በሚሊዮን ብር በመሸጥ የሚጠቀሙ በመኖራቸው እንዲሁም በኮርፖሬሽኑና በግል የንግድ ቤቶች ኪራይ መካከል ያለውን የኪራይ ተመን ልዩነት ለማስተካከልና ፍትሃዊ ለማድረግ ነው ።

የኮርፖሬሽኑን የፋይናንስ ምንጭ ለማሻሻልና አዳዲስ ቤቶችን ለመስራትና ቤት ለሌላቸው ቤት እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሆነ ኮፖሬሽኑ ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም