በጅግጅጋ ለሚከበረው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው

158

አዲስ አበባ ጥር 15/2011 ለስምንተኛ ጊዜ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለሚከበረው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለጸ።

የፎረሙ መካሄድ የከተማ ነዋሪዎችን፣ የመንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ እና ትብብር በማጠናከር የከተሞች ልማት ለማፋጠን የሚያስችል መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ካሳሁን ጎፌ ተናግረዋል።

በከተሞች የደህነትና መልካም አስተዳደር ችግርን በማቃለል ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር ለማድረግ እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

ከተሞችን እርስበርስ ለማስተዋወቅና ለመማማር ዕድል ለመፍጠር፣ ለገፅታ ግንባታ፣ ኢንቨስትመንትና ንግድን ለማጠናከር እንደሚያግዝም አብራርተዋል።

ለቱሪዝም ፣ ታሪካዊ ፣ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች ለማስተዋወቅም ያግዛል ነው ያሉት።

የከተሞች ልማት ላይ ለተሳተፉ ዕውቅና የሚሰጥ ሲሆን አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን ለማበረታታት እና የእርስ በስር ውድድርን በከተሞች መካከል ለማካሄድ የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

በጅግጅጋ ከተማ 14 ሄክታር መሬት ቦታ ለከተሞች የኤግዝቢሽን ማሳያ እና ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ  ሲሆን ከተሞች መልዕክታቸውን በተለያዩ ፎቶግራፎች፣ ዘጋቢ ፊልሞች፣ በ3ዲ ማሳያዎችና በሌሎችም የሚያቀርቡ ይሆናል።

በፎረሙ ላይ 200 ከተሞች ይሳተፋሉ ተብሎ ሲጠበቅ እስካሁን 109 ከተሞች ተመዝግበዋል። ምዝገባውም እስከ ጥር 25 ቀን 2011 ዓ.ም ይቀጥላል።

በ515 ሞዴል ኢንተርፕራይዞች መካከል ውድድር ይደረጋል፣ 23 የተለያዩ ጽሁፎች ይቀርባሉ፣ በየቀኑ አራት የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ተሳታፊ እንግዶች ይሳተፋሉ፣ የሙዚቃ ኮንሰርትም ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የሶማሌ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዱልፈታ ሼህቢሂ የጅግጅጋ ከተማ ፎረሙን ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ የጸጥታ ስጋት እንደሌለና የፌዴራል፣ የክልልና የአጎራባች ክልሎች የጸጥታ አካላት በጥምረት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ በሶማሌ ክልል መንግስት እና በጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር አዘጋጅነት የሚካሄደው ስምንተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከየካቲት 9 እስከ 14 ቀን 2011 ዓ.ም "መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከሁለት ሺህ በላይ ከተሞች እንዳሉ ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም