ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ዕቅድ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ይተገበራል

112

አዲስ አበባ ጥር 15/2011 ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ዕቅድ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ተገለጸ።

የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንና ዓለም አቀፉ የዘላቂ ልማት ተቋም በጋራ በዕቅዱ ዙሪያ ያዘጋጁት ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2010 በሜክሲኮ ካንኩን ከተማ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አገራት ከዚህ በፊት የነበራቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊስና ስትራቴጂ መሰረት አድርገው የየራሳቸውን ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ዕቅድ ለማውጣት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

በዚሁ መሰረት አገራቱ የደረሱበት ስምምነት "የካንኩን የአየር ንብረት ማጣጣሚያ የዕቅድ ስርዓት" የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን የማጣጣሚያ ዕቅዱ ከሶስት ዓመት በፊት የተፈረመው የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አካል ነው።

በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያም በመስከረም 2010 ዓ.ም ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ዕቅድ ይፋ ማድረጓ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ዕቅዱን ለመተግበር የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ደባሱ ባይለየኝ ገልጸዋል።

ባለፉት 16 ወራት የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ዕቅዱን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ እየተገበረች ያለው ፖሊስ፣ ስትራቴጂና መርሃ-ግብሮች መገምገማቸውን ተናግረዋል።

ግምገማውን መሰረት አድርጎ የትኩረት አቅጣጫዎችን የመለየትና የማስቀመጥ፣ በዕቅዱ ዙሪያ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች በመውረድ ውይይቶች መደረጋቸውንና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን አመልክተዋል።

ዕቅዱ የማይገበር የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ስትራቴጂን መሰረት ያደረገ እንዲሆን መደረጉን አንስተዋል።

በዚሁ መሰረት ዕቅዱ በስትራቴጂው ላይ በተቀመጠው መሰረት የአየር ንብረት ለውጥ ስራ ላይ ያለውን ችግር ብቻውን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት በቂ ባለመሆኑ ከሌሎች ዘርፎች ጋር የማቀናጀት ስራ እንደተከናወነም ጠቅሰዋል።

ግብርናና፣ የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደርና መሰረተ ልማት ከአየር ንብረት ለውጥ ስራው ጋር የተቀናጁ ዘርፎች መሆናቸውንና የአየር ንብረት ለውጥ ስራው አሳታፊ፣ የተቀናጀ ምላሽ መስጠት፣ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግና የቅንጅት አሰራር ማጎልበት የዕቅዱ ዋነኛ ሀሳቦች ናቸው ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተቋማት የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች የሚፈቱበትን አቅም ማጠናከርና አጋር አካላት መደገፍ የሚችሉበትን መዋቅር ማዘጋጀት ሌሎች የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑም ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት በተያዘው ዓመት ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ዕቅድ የሚሆን ፍኖተ ካርታና የገንዘብ ስትራቴጂ እንደሚዘጋጅ አመልክተዋል።

ሁለቱ ስራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ በ2012 ዓ.ም ዕቅዱ ተግባራዊ እንደሚሆንና እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር እስከ 2030 እንደሚቆይም ነው አቶ ደባሱ ያስረዱት።

ዓለም አቀፉ የዘላቂ ልማት ተቋም የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያ ሚስ አንጊ ዴዝ በበኩላቸው እስካሁን 11 አገራት ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ዕቅዳቸውን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስገባታቸውን ጠቁመዋል።

ሌሎች 64 አገራት ዕቅዳቸውን የማዘጋጀት ሂደት ላይ እንደሚገኙና ኢትዮጵያም ከነዚህ አገራት ውስጥ እንደምትጠቀስ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የዘላቂ ልማት ተቋም ኢትዮጵያ ዕቅዱን ተግባራዊ እንድታደርግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ዕቅድ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ስራቸውን ከልማት ፖሊስና ስትራቴጂያቸው ጋር በማቀናጀት ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ችግሩን መፍታት ያስችላል ብለዋል።

ዕቅዱን ለማስፈጸም ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግና ገንዘቡ ከመንግስት፣ ከግሉ ዘርፍና ከአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች እንደሚሰበሰብ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም