የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ አለባቸው - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

67

አዲስ አበባ ጥር 15/2011 በግንባታ ላይ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደረጃቸውን ጠብቀው በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ሲል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን ፓርኮችን የማልማትና የማስተዳደር ስራዎች አፈጻጸምን ዛሬ ገምግሟል።

በዚህም ምክር ቤቱ ኮርፖሬሽኑ በተለይ የተጀመሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተያዘላቸው ጊዜ ደረጃቸውን ጠብቀው እንደጠናቀቁ መሰራት እንዳለበት አሳስቧል። 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሃመድ ዩሱፍ እንደገለጹት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተያዘላቸው ጊዜ በሚፈለገው የጥራት ደረጃ ከማጠናቀቅ አንጻር ውስንነቶች አሉ።

ለአብነትም የድሬዳዋ፣ የቂሊንጦ፣ የባህር ዳር፣ የደብረ ብርሃን፣ የአረንቲ እና የአይሻ/ደወሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው የተጓተቱ ፕሮጀክቶች ናቸው።

በፓርኮች የሳይት መረጣ፣ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በቋሚነት በቦታው ላይ ሆኖ የመከታተልና የመቆጣጠር ስራ፣ በግንባታ ላይ የሚሳተፉ ተቋራጮችና አማካሪ ድርጅቶች የማስፈጸምና የቅንጅት ክፍተት መኖሩን አመላክተዋል።

በዚህም በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲለሙ የተፈለጉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና በተቀመጠላቸው የጥራት ደረጃ ተጠናቀው ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸው ገልጸዋል። 

በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተገቢው ሁኔታ በማልማት፣ የኢንዱስትሪ እድገት እንዲስፋፋ፣ የኤክስፖርት ምርት እንዲያድግና ለዜጎችም ምቹ የስራ እድል እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ የተጠናከረ ስራ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ለሊሴ ነሜ በበኩላቸው ኢንቨስተሮችን የመሳብ አቅም ዝቅተኛ መሆን፣ የኃይል አቅርቦት ችግር መኖር፣ ለልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ በጊዜ አለመፈጸምና ሌሎችም የሎጅስቲክ ችግሮች በግንባታ ላይ ያሉና የተጓተቱትን ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ለመገንባት እክል መፍጠሩን ተናግረዋል።   

ይሁንና ባሉት ችግሮችም ቢሆን ባለው አቅም  በአገሪቷ ከተገነቡ 11 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ስድስቱ ተጠናቀው ወደ ስራ መግባት መቻላቸውን ጠቁመዋል።

የአዳማ፣ ሀዋሳ፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ ኮምቦልቻ እና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ስራ የገቡ ናቸው።

ኮርፖሬሽኑ በቀጣይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ግንባታቸው የተጓተቱትን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅና ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ የተጠናከረ ስራ እንደሚሰራ የገለጹት ስራ አስፈጻሚዋ፤ የድሬዳዋ፣ ቂሊንጦ፣ የባህር ዳርና ደብረ ብርሃን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ በሚገኙ 11 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ45ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን ፓርኮቹ በየወሩ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ከኤክስፖርት ገቢ እያስገኙ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም