የጤና ሚኒስቴር በጤና ጣቢያዎች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል እየሰራ ነው

104

አዲስ አበባ ጥር 15/2011 የጤና ሚኒስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ የሪፈራል ሆስፒታሎችን ጫና ለመቀነስ በጤና ጣቢያዎች የሚሰጠውን የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት አፈጻጸም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።

ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት በአገሪቱ ባሉ ሪፈራል ሆስፒታሎች ያለውን ጫና ለመቀነስ በመሰራት ላይ ነው።

በመሆኑም የጤና ጣቢያዎችን የመሰረተ ልማት፣ የሰው ኃይል ግንባታ ጥራት መጓደል፣ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረትና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ጥረት በመደረግ ላይ ነው ብለዋል።

በሆስፒታሎች ተኝተው የሚታከሙ ህሙማን ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በሆስፒታሎች ወለል ላይ ተኝተው የሚታከሙ መኖራቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ አሁን ግን የበጀቱን 80 በመቶ የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና አገልግሎትን ለማሻሻል እየዋለ ነው ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና አገልግሎቶች በጤና ጣቢያ በተገቢው መንገድ ስለማይሰጡ በሆስፒታል ደረጃ በሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች ላይ ጫና እየፈጠረ ነው።

በአንዳንድ ሆስፒታሎች የሚገኙ አልጋዎች በነፍሰጡር እናቶች የሚያዙ ሲሆን እንደ ካንሰር ያለ ህክምናን በሚፈለገው መጠን ለማከም እንዳልተቻለም ገልጸዋል።

የጤና ጣቢያዎችን አቅም ለማጠናከር ባለፉት ስምንት ወራት 452 ጤና ጣቢያዎች በሶላር ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን በጤና ጣቢያዎቹ የቀዶ ህክምናን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ማሻሻል እንደተቻለም አስረድተዋል። 

በ400 ጤና ጣቢያዎች ተጨማሪ የቀዶ ህክምና ክፍሎች የተገነቡ መሆናቸውን ዶክተር አሚር ገልጸዋል።

የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲጠናቀቅ ''የመብራትና ውሃ አገልግሎቶች፣ ባለሙያዎችና መሰረታዊ የላብራቶሪ መሳሪያዎችን ያላሟላ አንድም ጤና ጣቢያ እንዳይኖር ለማድረግ ዓላማ ይዘን እየሰራን ነውም'' ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ያስቀመጠውን ዕቅድ ስኬታማ በማድረግ በሪፈራል ሆስፒታሎች የሚታየውን ጫና በመቀነስ በሆስፒታል ደረጃ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ጥራት ማሻሻል እንደሚቻልም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም