በዳራ ማሎ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት አለፈ

120
አርባምንጭ ግንቦት 19/2010 በጋሞ ጎፋ ዞን ዳራ ማሎ ወረዳ ትናንት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተፈጠረው የመሬት መንሸራተት አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ፡፡ አደጋው የተከሰተው በወረዳው በተለምዶ "ጮዬ"  የተባለው ዳገታማ ስፍራ መሬቱ በዝናቡ ኃይል ተቆርጦ በመንሸራተቱ መሆኑን  የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢያሱ አፈወርቅ ለኢዜአ ገልጸዋል። ከዳገቱ በጭቃ ተቀላቅሎ የወረደው አፈር የሶስት አባወራዎችን  ቤቶች ማስጠሙን ተከትሎ ቤት ውስጥ የነበሩ ዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል። ከሞቱት መካከል አምስቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ሲሆኑ፤ በወቅቱ ሌላ ቦታ የነበሩት የቤቱ አባወራ ብቻ ተርፈዋል፡፡ የአካል ጉዳትና የጤና መታወክ የደረሰባቸው 17 ሰዎች ደግሞ በወላይታ ሶዶ ሆስፒታልና ዋጫ ጤና ጣቢያ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን አቶ ኢያሱ አመልክተዋል። የሟቾች አሰከሬን ለቤተሰቦቻቸው መሰጠቱንም ጠቁመዋል። የጋሞ ጎፋ ዞን አደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ማዶረ በበኩላቸው በአደጋው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል፡፡ ተፈናቃዮችን ወደ ሌላ አካባቢ የማዛወርና መልሶ የማቋቋም ስራ መጀመሩንም አስረድተዋል። በአከባቢው እየጣለ ያለው ከበድ ዝናብ እስኪቀንስ ተጎጂ ቤተሰቦች የሚጠለሉበት ጊዜያዊ መጠለያ፣ ምግብና አልባሳት እርዳታ እየቀረበላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም