ኢትዮ-ቴሌኮም የሚያስተዋውቀው የ’ይሙሉ’ አገልግሎት ለካርድ ማሳተም የሚያወጣውን ወጪ 96 በመቶ ይቀንሳል

1350

አዲስ አበባ ጥር 15/2011ኢትዮ-ቴሌኮም የሚያስተዋውቀው የ’ይሙሉ’ አገልግሎት ለካርድ ማሳተምና ማሰራጨት የሚያወጣውን ወጪ 96 በመቶ የሚቀንስና ተጨማሪ የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን አስታወቀ።

የ’ይሙሉ’ አገልግሎት ውክልና የተሰጣቸው ነጋዴ ግለሰቦች ቴክኖሎጂውን ዘመናዊና ቀልጣፋ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም እንደሚለው፤ የአየር ሰዓትን ለመሙላት እያገለገለ ከሚገኘው ካርድ በተጨማሪ አዲስ ‘ይሙሉ’ የተሰኘ የኤሌክትሮኒክ አገልግሎትን ጎን ለጎን ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል።

ተቋሙ ካርድ ለማሳተም፣ ለማከማቸትና ለማሰራጨት በአማካይ በየአመቱ 500 ሚሊዮን ብር ወጪ ያወጣል።

በተቋሙ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ወይዘሪት ጨረር አክሊሉ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ አዲሱ አገልግሎት ተጠቃሚው ፍላጎቱ ሳይገደብ እስከፈለገው የብር መጠን መሙላት የሚያስችለው ነው።

ከዚህም ሌላ መንግስት ለካርድ ማሳተሚያና ተያያዥ ስራዎች የሚያወጣውን ወጪ 96 በመቶ የሚቀንስ ነው። 

ለኤሌክትሮኒክ ይሙሉ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ወደስራ ሲገባ በካርድ አማካኝነት የሚወጣውን 500 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ወጪውን ወደ 22 ሚሊዮን ብር ዝቅ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።

ከዚህም ሌላ ካርዱ ታትሞ የሚመጣው ከውጪ በመሆኑ የአገርን የውጪ ምንዛሪ ሊያድን የሚችል አጋዥ የአገልግሎት አይነት ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በካርድ ማከፋፈል ላይ የተሰማሩ ከህዳሴ ቴሌኮም ጀምሮ የተለያዩ ድርጅቶችና የተደራጁ ወጣቶች በአዲሱ አገልግሎት በተመሳሳይ መልኩ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተደረገ እንደሆነ ወይዘሪት ጨረር አስታውቀዋል።

የዚህ አገልግሎት ተደራሽነት እየሰፋ ሲሄድ ለወጣቱ ተጨማሪ የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል አዎንታዊ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል።

እስካሁን የይሙሉ አገልግሎት በጅምር ላይ ሲሆን በርከት ያሉ ውክልና ያላቸው ተቋማትና ግለሰቦች ወደ ስራ መግባታቸውን የኮሙኒኬሽን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

በሌላ መልኩ የይሙሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ ግለሰቦች የይሙሉ አገልግሎት ጥሩ ጅማሬ ሲሆን መስተካከል ያለበት ነገር እንዳለ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል።

የሸቀጥ ሱቅ ነጋዴው አቶ አሊ ኑረዲን ”አገልግሎቱ ከካርዱ ጎን ለጎን መሰጠቱ ካርድ የለም ተብሎ የሚመለስ ደንበኛ እንዳይኖር ቢያደርግም ከስራችን ፀባይ ጋር ሊመጣጠን የሚችል ፍጥነት የለውም” ብለዋል።

በይሙሉ የሚሰጠው ቦነስ በማለቁና አንዳንዴም በኔትወርክ አለመኖር ሂሳብ ለማስተላለፍ ስለሚዘገይ ተገልጋዩ የቀድሞውን ካርድ እንዲመርጥ አድርጓልም ነው ያሉት።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት አብዱሰላም በድሩ በበኩሉ ”ቴክኖሎጂው እንደጅምር ጥሩ የሚባልና ካርድ ለማምጣት የምናባክነውንም ጊዜ የቆጠበልን ነው” ብሏል።

ከዚህም ሌላ ለተጠቃሚዎች የሚሰጠው ማበረታቻ ጉርሻ ጥሩ ማበረታቻ ነው ባይ ነው።

እንደ ነጋዴዎቹ አስተያየት የይሙሉ አገልግሎት በተሳካ ሁኔታ ተግባር ላይ እንዲውል ጊዜ የሚወስድ የሆነው ሂደት በፍጥነት መሙላት ወደሚያስችል መተግበሪያ ቢዘጋጅለት መልካም መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህም ሌላ ለነጋዴዎች የሚታሰበው ጉርሻ ቢሻሻል አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።

ተቋሙ  በበኩሉ አዲሱ ቴክኖሎጂ  ገና በቅርብ ወደ ተግባር የገባ በመሆኑ ያሉ ችግሮችን በማስተካከል በመላው አገሪቱ ለማዳረስ እንደሚሰራ ተናግሯል።

አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ የሚፋቅ ካርድን ለማስቀረት ባይታሰብም በሂደት ግን ወደ ኤሌክትሮኒክ ለመቀየር ታስቦ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ አንፃር የኤሌክትሮኒክ ይሙሉ አገልግሎት እስከ ሰኔ ወር 50 በመቶውን የአየር ሰዓት መሙያ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።