በጋምቤላ ከተማ ዘጠኝ ኪሎ ግራም የዝሆን ጥርስና የጦር መሣሪያዎች ተያዙ

75

ጋምቤላ ጥር 15/2011 የፌዴራል ፖሊስ በጋምቤላ ከተማ ዘጠኝ ኪሎ ግራም የሚመዝን የዝሆን ጥርስና ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ከአንድ ተጠርጣሪ ጋር ትናንት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።

በፌደራል ፖሊስ የምዕራብ ዲቪዥን የሦስተኛ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ተረፈ በለጠ ለኢዜአ እንደገለጹት ዕቃዎቹ የተያዙት ለፖሊስ ከሕዝብ በደረሰ ጥቆማ ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በአንድ ግለሰብ ቤት ባደረገው ፍተሻ ነው።

ከዝሆን ጥርስ በተጨማሪ ሦስት ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችና 2 ሺህ 392 የክላሽና የብሬል ጥይቶች ይገኙበታል።

በተጠርጣሪው ላይ በተደረገው ማጣራትም በቁጥጥር ሥር የዋሉት የጦር መሣሪያዎችና የዝሆን ጥርስ ከጎረቤት አገር እንደመጡና ወደ አካባቢው ከተሞችና መሃል አገር ሊጓጓዙ እንደነበር መረጋገጡን ተናግረዋል። 

 በአሁኑ ወቅት በተጠርጣሪው ላይ ማስረጃ የማሰባሰብ፣ የማጣራት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ያመለከቱት የምርመራ ሂደቱ እንደተጠናቀቀም ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ይላካል።

ክልሉ ከአጎራባች  አገሮችጋር ሰፊ የድንበር ወሰን ያለውና ከድንበር ዘለል የፈላታ አርብቶ አደሮች ወደ ክልሉ ከመግባታቸው ጋር ተያይዞ ሕገ-ወጥ  የጦር መሣሪያዎች ዝውውር መበራከቱን ገልጸዋል።

ፖሊስ ከክልሉና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለማስቆም እየሰራ ነው ብለዋል።

 የገቢዎች ሚኒስቴር የጋምቤላ መቅረጫ  ጣቢያ የኮንትሮባንድ መካላከል ቡድን መሪ ኢንስፔክተር ኡቻንግ ኡጁሉ ሕዝቡ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች በአገሪቱም ሆነ በሕዝብ ላይ የሚያስከትሉትን ችግር ለመከላከል ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በክልሉ በቅርቡ ወደ 80 የሚጠጉ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች፣የጥይቶችና የገንዘብ ኖቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም