የዘንድሮው የመከላከያ ሰራዊት ቀን በአዳማ ከተማ ይከበራል

81

አዲስ አበባ ጥር 15/2011የመከላከያ ሰራዊት ቀን ሲከበር ኢትዮጵያ ከጸጥታ ችግር ተላቃ የተጀመረው አገራዊ ለውጥ ግቡን እንዲመታ ሰራዊቱ ቃሉን የሚያድስበት እለት እንደሚሆን የሰራዊቱ ኢንዶክትርኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል መሃመድ ተሰማ አስታወቁ።

ዋና ዳይሬክተሩ በበዓሉ፤ ህዝቡና ሰራዊቱ በጋራ የሚመክሩበት አገራዊ የፓናል ውይይት እንደሚደረግም አክለዋል።

ሜጀር ጀኔራል መሃመድ ተሰማ ይህን ያሉት "ህገመንግስታዊ ታማኝነትና ህዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን" በሚል መሪ ሃሳብ ለሰባተኛ ጊዜ የሚከበረውን የአገር መከላከያ ሰራዊት ቀንን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

በዓሉ በኢፌዴሪ አየር ኃይልና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት የካቲት 7 ቀን 2011ዓ.ም በአዳማ ከተማ በአገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።

ሜጀር ጀኔራል መሃመድ ተሰማ ሰራዊቱ ህዝባዊነቱን ማጎልበት የበዓሉ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል።

መሪ ሐሳቡን መሰረት በማድረግም የበዓሉን ዓላማ ለማሳካት የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከናወኑ ጠቁመው፤ በፌዴራልና በሁሉም ክልሎች ርእሰ መስተዳደር የሚመሩ ህዝባዊ ውይይቶች እንደሚደረጉም ለአብነት አንስተዋል።

በውይይቱ ሰራዊቱ ወደፊት ምን ላይ ማተኮር እንዳለበት አቅጣጫ የሚሰጡ ግብዓቶች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተናገሩት።

ከፓናል ውይይቱ በተጨማሪም ሰራዊቱ  በየደረጃው በግዳጅ አፈጻጸም ወቅት ስለነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች የሚወያይበት መድረክ አንደሚዘጋጅም ተናግረዋል።

በዕለቱ በተለያዩ የጦር ክፍሎች የመከላከያ ሰራዊቱን ተልዕኮ የመፈጸም ዝግጁነት የሚያሳዩ ወታደራዊ ትርዒቶችና ስፓርታዊ ውድድሮች እንደሚደረጉም አክለዋል።

የዘንድሮው የመከላከያ ሰራዊት ቀን ኢትዮጵያ በአገራዊ ለውጥ ውስጥ ሆና የሚከበር በመሆኑ ልዩ አንደሚያደርገው የገለጹት ሜጀር ጀኔራሉ፤ ሰራዊቱ  በዓሉን ሲያከብር  ኢትዮጵያ ከጸጥታ ችግር ተላቃ ለውጡ ግቡን እንዲመታ ቃሉን እንደሚያድስ አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር በነበረችበት ያለፉት ሁለት ዓመታት በዓሉ በአገር አቀፍ ደረጃ  በደማቅ ሁኔታ ያልተከበረ ሲሆን፤ በ2007 ዓ.ም ግን በምዕራብ እዝና በአማራ ክልል አዘጋጅነት በዓሉ በአገር አቀፍ ደረጃ በባህር ዳር በደማቁ መከበሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም