የግንቦት ሃያን በዓል አዎንታዊ እይታን በሚያስታጥቁ መልካም ተግባራት አጅቦ ማክበር ይገባል-የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

69
አዲስ አበባ ግንቦት 19/2010 ኢትዮጵያውያን 27ኛውን የግንቦት ሀያ የድል በዓል አዎንታዊ እይታን በሚያስታጥቁ መልካም ተግባራት አጅበው እንዲያከብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ ጠየቁ። "የአርበኝነት፣ የድል፣ የትግል እና የአይበገሬነታችን ተምሳሌት የሆኑ ብሄራዊ በዓሎቻችንን በምናከብርበት ወቅት ከክበረ-በዓልነት ባሻገር የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ተላብሰን መሆን አለበት" ሲሉም አስገንዝበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገ የሚከበረውን 27ኛውን የግንቦት ሃያ በዓል አስመልክተው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስላልፈዋል። በመልዕክታቸውም "የድል በዓሉን ስናከበር ከውስጣችንም ሆነ ከውጪያችን አስታርቀውን ለራሳችንም ሆነ ለሌላው አዎንታዊ እይታን በሚያስታጥቁን መልካም ተግባራት ታጅበን መሆን ይኖርበታል፤" ሲሉ አሳስበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ መላው ዜጋ ሊያከናውናቸው ይገባሉ በማለት ስድስት አንኳር ጉዳዮችን በዘረዘሩበት በዚሁ መልዕክታቸው "ሁሉም ሰው ከራሱ ጋር ተፈላልጎ ለመገናኘት ግንቦት ሀያ የጥሞና ጊዜ ሊሆነው ይገባል'' ብለዋል። አክለውም "አካባቢን ለመረዳትም ሆነ ለመግራት ወደውስጣችን በመመልከት ከራስ ጋር በሚደረግ እርቅ እና የጥሞና ሰዓት ነፍሳችንን በአዎንታዊ ኃይል መሙላት እጅጉን ወሳኝ ልምምድ መሆን አለበት፤" ሲሉም መክረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ "ይህች የምንሳሳላትና የምንወዳት አገራችን ሰላም የምትሆነው፣ ጋራ ሸንተረሯ የሞት ሲላ የሚዞረው ሳይሆን በሰላም ምሳሌዎቹ እርግቦች ጣፋጭ ዜማ ዙሪያ ገባው የሚደምቀው፣ ከራሳችን ጋር ስንታረቅ፤ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ይቅር ስንባባል ብቻ ነው፤" ብለዋል። በመሆኑም የግንቦት ሃያ የድል በዓል በሚከበርበት እለት በተለያዩ ምክንያቶች የተኳረፉ ወዳጆች፣ ጎረቤታሞች፣ የትዳር አጋሮች ወዘተ ይቅር በመባባል ሰላም እንዲያወርዱ ጠይቀዋል። ኢትዮጵያውያን ክብረ በዓላትን ሲያከብሩ ከጎረቤቶቻቸው፣ ከቅርብና ሩቅ ወዳጆቻቸው ጋር ያሉ ክፍተቶችን በእርቅና በይቅርታ የማከም የጋራ ባህል ማዳበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል። ክብረ በዓሉ የመልካምነት፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የሰላም መታገያ እንዲሆን ከራስ አልፎ እስከ አገር የሚዘልቅ የፍቅር፣ ሰላምና የመረዳዳትን ባህል በማጎልበት መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል። ህብረተሰቡ የማንበብ፣ የመመርመርና ከሚታየው ሁነት ጀርባ የሚኖረውን እውነት የማጥናት የዘመናት ልምምድ ያለው ህዝብ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በዓሉን ስናከብር አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር፣ በማንበብ እውቀትን በውስጣችን ለማሰባሰብ በመወሰን ቢሆን እጅጉን እናተርፋለን፤" ሲሉ ተናግረዋል። በዓሉ ሲከበር የማወቅ፣ የመሰልጠን፣ የማደግና የመዘመን ምልክት ለሆነው አካባቢ ትኩረት በመስጠት መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም