በጥረት ኮርፖሬት በሃብት ብክነት የተጠረጠሩት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ተያዙ

80

ባህር ዳር ጥር 15/2011 በጥረት ኮርፖሬት ከህግና መመሪያ ውጭ ግዥ በመፈፀም የሃብት ብክነት ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዝጋለ ገበየሁ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የጥረት ኮርፖሬት አክሲዎን ማህበሩ ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች በአምስት ካምፓኒዎች ላይ በተደረገ የሒሳብ ምርመራ የሃብት ብክነት ማድረሳቸው ተረጋግጧል።

እስካሁን በአምስት ካምፓኒዎች ላይ የተደረገ የሒሳብ ምርመራ የተጠናቀቀ ሲሆን በሁለት ካምፓኒዎች ላይ የሚካሄደው የሒሳብ ምርመራም በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ባህር ዳር ሞተርስ፣ ላፓልማ፣ ኢስታንቡል ጋዝ ማምረቻ፣ በየዳ ሰስቴኔብል ኬሚካል ማምረቻና ደሴ መጠጥ ውሃ ማምረቻ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማህበራት የሒሳብ ምርመራ የተደረገባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ኮሚሽነር ዝጋለ ገለጻ ለእነዚህ አክሲዎን ማህበሮች 77 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግዥ የተፈፀመ ቢሆንም ከዚህ ውስጥ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ያለአግባብ  ክፍያ ተፈፅሞ መገኘቱን አብራርተዋል።

"ይህ ገንዘብ የወጣባቸው አክሲዎች ማህበራት ስራም አልጀመሩም፤ ለማህበራቱ ተብለው የተገዙ ንብረቶችም ካለአግባብ ለብልሽት ተዳርጎ ተገኝቷል" ብለዋል።

የዳሸን ቢራ ፋብሪካና የዱቤቱስ አክስዮን ማህበር በሒሳብ ምርመራ የማጣራት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።

በመሆኑም ማህበሩን በከፍተኛ ኃላፊነት ይመሩ የነበሩት ሁለቱ ግለሰቦች የካምፓኒዎቹን የአዋጭነት ጥናት ሳይካሄድ ግዥ እንዲፈፀም በማድረግ በህዝብ ሃብት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው በመረጋገጡ በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል።

" ከእዚህ በተጨማሪ ከፋይናንስ ህግና ደንብ ውጭ በግለሰቦች ውሳኔ ብቻ ብድር ለግለሰቦችና ለድርጀቶች ሲሰጥ መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል" ብለዋል።

በመሆኑም ሙስናውን በዋናነት አንቀሳቅሰዋል የተባሉ ሁለቱ ግለሰቦች በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ ለማድረግ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በቀጣይም ከእነሱ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት ያላቸውን አመራሮችም ሆነ ግለሰቦችን በማጣራት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የሚደረግ መሆኑን አቶ ዝጋለ አመልክተዋል።

የሁለቱ ተጠርጣሪ ግለሰቦች የህግ ጉዳይ በክልሉ የሚታይ መሆኑን ጠቁመው፣ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የክልሉ የፖሊስ ኃይል ከፌደራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ መሰራቱን አስታውቀዋል።

በጥረት ኮርፖሬት ላይ የተጀመረው የማጣራት ሥራም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነር ዝጋለ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም