ኢትዮጵያና ጀርመን በቁልፍ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

57

አዲስ አበባ ጥር 15/2011 ኢትዮጵያና ጀርመን በቁልፍ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሂሩት በቤልጂዬም - ብራሰልስ በተካሄደው የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት የሚኒስትሮች ስብሰባ ወቅት ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚሼል ማንትፈሪንግ ጋር ተወያይተዋል።

በኢትዮጵያና ጀርመን መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጎልበት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ በስፋት ተወያይተዋል ነው የተባለው።

ከዚህም በተጨማሪ የጀርመን ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዋልተር ስቴይንሚዬር በሚቀጥለው ሳምንት በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት የሁለቱን አገሮች የቢዝነስ ግንኙነት ያሳድጋል ተብሎም ይጠበቃል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ እንዳሉት፤ የጀርመን ፕሬዘዳንት በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው የሁለቱን አገሮች የንግድና ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ያሳድጋል።

ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ስቴይንሚዬር ወደ ኢትዮጵያ ይዘዋቸው የሚመጡት የቢዝነስ ልዑካን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱን በስፋት እንደሚሰሩበት በር ይከፍታል።

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚሼል ማንትፈሪንግ በበኩላቸው በፕሬዝዳንቱ የሚመራው የልዑካን ቡድኑ የጀርመን ትልልቅ ኩባንያዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሄውም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባለው ነፃ የኢኮኖሚ ዘርፍ ለመሳተፍ ሰፊ እድል ይፈጥራልም ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ ከዓለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር ሀሪየት ባልድዊን ጋርም ውይይት አድርገዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሩ ሂሩት ኢትዮጵያና እንግሊዝ ያላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት መልካም መሆኑን አድንቀዋል።

እንግሊዝ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያላት ተሳትፎ ውጤታማ መሆኑን እንዲሁም በኢትዮጵያ ያለውን ቀጣይ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተሃድሶ አፅንዖት ሰጥተው ተወያይተዋል።

ሚኒስትር ሀሪየት ባልድዊን በእንግሊዝ በሚካሄደው የእንግሊዝ አፍሪካ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል።

ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሪ ሂሩት ከሮማንያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞኒካ ጎራሪይታ ጋርም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጎልበት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ ከምስራቅ አውሮፓ አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸውላቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሞኒካ ጎራሪይታም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትቸውን ግንኙነት ማሳደግ እንደምትፈልግ ገልጸው፤ በአዲስ አበባ ያሉ ሚሲዮኖቿን ወደ አምባሳደርነት ደረጃ ማሳደግ እንደምትፈልግም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም