ቦኽራ የአርሶ አደሮች ኅብረት ሥራ ዩኒዬን እሴት የተጨመረባቸውን የግብርና ምርቶች ወደ ገበያ ማቅረብ ጀመረ

68

ማይጨው ጥር 15/2011 በትግራይ ደቡባዊ ዞን የሚገኘው የቦኽራ የአርሶ አደሮች ኅብረት ሥራ ዩኒዬን እሴት በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ ማቅረብ ጀመረ።

ዩኒየኑ ያስገነባቸው የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ማምረት ጀምረዋል።

የዩኒዬኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ አታክልቲ ከበደ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በዩኒየኑ የተገነቡት የወተት፣ የእንስሳት መኖና የዳቦ ዱቄት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ወደ ምርት ገብተዋል፡፡

የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካው በሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ መገንባቱን ያስረዱት ሥራ አስኪያጁ፣ በቀን 8 ሺህ ሊትር ወተት የማቀነባበር አቅም አለው።

በቀን 200 ሊትር ወተት በማቀነባበርና በማሸግ ወደ ገበያ ማቅረብ እንደጀመረም ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካው የቅቤ፣የእርጎና የአይብ ምርቶችን በተለያየ መጠን በማሸግ ወደ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው የወተት ምርት ማሰባሰቢያ ማዕከላት በአምስት ቀበሌ ገበሬ ማህበራት መክፈቱንና ከአምስት የወተት አምራች ኅብረት ሥራ ማህበራትም ውል መፈራረሙን አስታውቀዋል፡፡

የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ወደ ምርት መግባቱን አቶ አታክልቲ ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካው የተለያዩ እንስሳት መኖዎችን ጨምሮ  በሰዓት እስከ 15 ኩንታል ሞላሰስ እያመረተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው በዞኑ የሚታየውን የእንስሳትን የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት እጥረት ያቃልላል ብለዋል፡፡

ለወተት ላሞች፣ ለበጎች፣ለጫጩትና ለእንቁላል ዶሮ መኖ ለኅብረተሰቡ እያቀረበ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡

ዪኒየኑ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባገኘው የ6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ በቅርቡ ማምረት ይጀምራል ብለዋል፡፡

ፋብሪካው በአካባቢው በስፋት የሚመረተውን የስንዴ ምርት ተጠቅሞ በቀን 420 ኩንታል የዳቦ ዱቄት በማምረትና በማሸግ ለአካባቢው ገበያ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

በእንዳ መሆኒ ወረዳ የመኻን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አሰፋ ግርማይ ከአሁን ቀደም የሚያመርቱትን ወተት ከቤተሰብ ፍጆታ አልፎ ለገበያ የማይቀርብ  እንደነበር ገልጸው፣አሁን ፋብሪካው ለአንድ ሊትር 18 ብር በመክፈል በገቢው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

ይህም የእንስሳት ርባታውን በተሻለ መንገድ ለማካሄድ  እንዳስቻላቸው አመልክተዋል፡፡

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዝናቡ ካህሳይ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያው ሥራ መጀመር እንቁላል ጣይ ዶሮዎቼን ጥራጥሬ ብቻ በመቀለብ የማገኘውን ምርት ለማሳደግ አስችሎኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም