ኅብረተሰቡ በድግስ ሀብቱን ከማባከን ወጥቶ ቁጠባን ባህሉ እንዲያደርግ ተጠየቀ

78

ሽሬ እንዳስላሴ ጥር 14/2011 ኅብረተሰቡ ከአቅም በላይ በመደገስ ሀብትን ከማባከን ይልቅ፤ቁጠባን ባህል ለማድረግ ትኩረት እንዲሰጥ የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች አሳሰቡ።

የከተማው የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በተለያዩ ምክንያቶች ከአቅም በላይ በመደገስ የሚወጣውን ገንዘብ ለራስና ለአገ በሚጠቅም መልኩ ማዋል ይገባል።

በተለይ አርሶ አደሩ ያገኘውን ከምርቱ የሚያገኘውን ሀበት በአግባቡ በመጠቀም ከኋላቀር አስተሳሰብና ከፉክክር መንፈስ እንዲወጣ መክረዋል።

በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የታሕታይ አዲያቦ ወረዳ ነዋሪ አቶ መድህን ገብረእግዚብሔር ልጃቸውን ለመዳር ባለፈው ዓመት ከ23 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ።

ሀብታቸውን አሟጠው ለሠርግ በማዋላቸው በዓመቱ በዝናብ እጥረት በአካባቢያቸው የተከሰተውን ድርቅ መቋቋም ተስኗቸው ለእርሻ የሚገለገሉባቸውን ሁለት በሬዎቻቸው መሸጣቸውን ተናግረዋል።

''ለአንድ ሰሞን ዝና ተብሎ ለዓመታት የተከማቸ ሀብትን ለአንድ ቀን ድግስ ማውጣት ለዓመታት መስቃየትን እንደሚያስከትል የአካባቢው ሕዝብ ከእኔ መማር አለበት'' ባይ ናቸው።

ከደደቢት የብድርና ቁጠባ ተቋም የወሰዱትን 15ሺህ ብር ሰርቶ ለማትረፍ ሳይሆን፤ለልጃቸው ምረቃ በማዋላቸው ብድሩን ለመመለስ መቸገራቸውን የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ምጽላል ልጅዓለም ናቸው።

በባዕድ አገር ሰርቶ ያጠራቀሙትን ሀብት ከሞተ ረጅም ዓመታት ላስቆጠረ ዘመድ ተዝካር ማውጣት አስፈላጊ እንዳልሆነም የዞኑ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች መክረዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረእድ ተስፋይ ተወልደ እንደገለጹት፣''ሰው ምን ይለኛል ከሚል አጉል እምነት በመነሳት አቅምን ያላገናዘበ ድግስ ማዘጋጀት ኩነኔን እንጂ ፅድቅን አያመጣም።''

''ምክንያቱም አላስፈላጊ ወጪ በማውጣት የተራቆተ ቤት ለችግር ሲጋለጥ ፈጣሪውን ሲለምን ይታያልና'' ሲሉም ያክሉበታል።

‘’ሀብት ያለው ሰው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚኖሩ ወገኖቹ አቅም የፈቀደውን ድጋፍ ማድረግ እንጂ፤ አላስፈላጊ ወጪ በማውጣት መደገስ የእስልምና ኃይማኖት መርህ አይደለም’’ ያሉት ደግሞ የእስልምና እምነት አባት ሼክ መሐመድ አማን መሐመድ ናቸው።

ሠርግ ለማንኛውም ሙስሊም ኅብረተሰብ አስፈላጊ ቢሆንም ከአንድ በግ ያልበለጠ ከ50 ሰዎች ያልዘለሉ ታዳሚዎች በመጥራት እንዲደገስ ሃይማኖቱ ይፈቅዳል ብለዋል።

ነገር ግን ሃይማኖቱ የማይፈቅደው ከአንድ በሬ በላይ ማረድ፣ፈፅሞ የማይደረገውን ከ10 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ የሙዚቃ ባንድ ሀብት ሲባክን እንደሚስተዋል ገልጸዋል።

የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የአገር ሽማግሌ አቶ አረጋይ አየለ ''ለልጆች ማቋቋሚያ ሳናስቀምጥ ያለንን ሃብት አሟጥጠን ለድግስ ማዋል የትውልድ ተወቃሽ ያደርገናል''ይላሉ።

''ድል ያለ ድግስ ደግሻለሁ ብሎ ከመመፃደቅ ይልቅ ለልጆቼ የወደፊት ሕይወት ምን ያህል ሃብት አስቀመጥኩኝ ማለቱን ይበጃል”ሲሉም ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

ሌላው የከተማው የአገር ሽማግሌ አቶ በላይ ፀሐዬ፣''የዛሬውን ሳይሆን፤ የነገውን ማየት ነው የሚበጀው።ምክንያቱም ዛሬ ላይ ሆነን ነገን ካላሰብነው ዛሬውን የያዝነው ለዛሬ ብቻ ነው የምናደርገው። ይህም ራዕይ አልባ ያደርገናልና'' ብለዋል።

የዞኑ አስተዳደር የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ክብሮም ብስራት ጉዳዩን አስመልክተው እንዳሉት፣ነዋሪዎች ያፈሩትን ሀብት በቁጠባ መጠቀም እንጂ፤ ላላስፈላጊ ድግስ ማዋል እንደማይገባቸው አመልክተዋል።

በብከነቱ ዋነኛ ተጎጂዎች ራሳቸው መሆናቸውን በማጤንም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም