ሠላምና የአገር ግንባታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የሥዕል አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፈተ

61

አዲስ አበባ ጥር 14/2011 ''ሠላም በተለምዶ ከምናውቀው የግጭት ወይም የሁከት መኖር አለመኖር የተሻገረ፤ የሰፋና የጠለቀ ትርጓሜ አለው'' ሲሉ የሠላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ። 

ሠላምና የአገር ግንባታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የሥዕል አውደ ርዕይ ዛሬ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል። 

የሠላም ሚኒስቴር በአገሪቷ የሰላም እሴቶች እንዲጎለብቱ የጀመረው ጥረት እውን እንዲሆን ከባለሙያዎችና ተቋማት ጋር ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩም ተገልጿል።  

ዛሬ የተከፈተው አውደ ርዕይም የዚሁ ጥረት አካል ሲሆን ከጥር እስከ 16 እንደሚቆይም ለማወቅ ተችሏል። 

የሠላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ወቅት ''ሠላም በተለምዶ ከምናውቀው የግጭት ወይም የሁከት መኖር አለመኖር የተሻገረ፤ የሰፋና የጠለቀ ትርጓሜ አለው'' ብለዋል። 

''በእያንዳንዳችን እጅ ከሚገኘው የውስጥ ሠላም፣የማህበረሰብ ሠላም፣ከተፈጥሮ እንዲሁም ከፈጣሪ ጋር እስካለው ሠላም ተደምሮ ዘላቂ የአገር ሠላም ይይዛል፤ ለዚህ ደግሞ መሰረት የሆነውን የራስ ሰላም ጭምር በተግባር ለመተርጎም እንዲህ አይነቱ የስነ-ጥበብ ዘርፍ ትልቅ አቅም አለው'' ነው ያሉት። 

ስነ-ጥበብ በተለይ ሠላምን በተመለከተ ጥልቅ ሀሳብ ማስተላለፍ የሚችል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ይህም የሠላም እሴቶች እንዲጎለብቱ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ነው ያመለከቱት። 

''ከራሱ ጋር የታረቀና ውስጣዊ ሰላም ያለው ሰው የህይወትን መተሳሰር የተገነዘበ ስለሆነ ከተፈጥሮ ጋር በሰላም ለመኖርና ለመታረቅ እድልም አቅምም ያላብሰዋል'' ሲሉም ተደምጠዋል።  

የግጭት ዋነኛ መንስኤ የሆነው 'እኔ ብቻ' የሚል አስተሳሰብ መወገድ እንደሚገባ የተናገሩት ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ መሰል አስተሳሰቦች እንዲቀየሩ በሙያችሁ የምታደርጉትን ጥረት ማጠናከር አለባችሁ በማለት አሳስበዋል። 

የሰዓልያንና ቀራጺያን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አክሊሉ መንግስቱ በበኩላቸው መንግስት ከእኛ ጋር ተቀራርቦ ቢሰራ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ አጋር ሆነን የበኩላችንን ለመወጣት ፍላጎት አለን ሲሉ ተደምጠዋል። 

''የስነ ጥበብ ትኩረት ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ናቸው፤ ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም ''ያሉት አቶ አክሊሉ፤ እነዚህን ስራዎች በአግባቡ ለማከናወን የቀለም፣ብሩሽ፣ ጋለሪና ስቱዲዬ ችግሮች መፈታት አለባቸው ብለዋል።  

አገራዊ ኃላፊነታችንን በአግባቡ እንድንወጣ መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግልን ይገባል የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።

የሠላም ሚኒስቴር ከሰዓልያንና ቀራጺያን ማህበር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው አውደ ርዕይ ላይ እውቅ ሰዓልያን ሥራቸውን አቅርበዋል።  

ለእይታ የቀረቡት የሥነ-ጥበብ ስራዎች የተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮችን የሚያሳዩ ሲሆን በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትን የሚያንጸባርቁ ናቸው።

የሕዝቡን ባህል፣አለባበስና ኃይማኖታዊ ይዘት የሚያሳዩ የሥነ-ጥበብ ስራዎች እንዲሁ ቀርበዋል። የጥበብ ስራዎቹ ሠላም የሁሉ ነገር መሰረት እንደሆነም ያስቃኛሉ።

በዕለቱ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ የአውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች ሠላምን በስዕል የመግለጽ መርሃ ግብር ላይም ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም