የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ለአባል አገራቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒካል ዳይሬክተሮች ስልጠና መስጠት ጀመረ

143

አዲስ አበባ ጥር 14/2011 የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ለአባል አገራቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒካል ዳይሬክተሮች  ስልጠና መስጠት ጀመረ።

ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆየው ስልጠናው በኮንፌዴሬሽኑ ዋና መቀመጫ ግብጽ ርዕሰ መዲና ካይሮ የሚሰጥ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ የ51 አፍሪካ አገራት እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒካል ዳይሬክተሮች እየተሳተፉበት እንደሚገኝ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒካል ዳይሬክተር አቶ መኮንን ብሩ በስልጠናው ላይ እየተሳተፉ መሆኑን የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ኢያሱ መርሃጽድቅ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ስልጠናውን የሚሰጠው የካፍ የቴክኒክና ልማት ኮሚቴ የአህጉሪቷ እግር ኳስ የበላይ ጠባቂ ተቋም የስራ ክፍል ሲሆን የአፍሪካን እግር ኳስ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ስልጠናው እንደሚያተኩር ገልጿል።

የአህጉሪቷ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒካል ዳይሬክተሮች የቴክኒካል እውቀታቸውን በማሳደግ ያገኙትን ተሞክሮ ለታዳጊ ቡድን አሰልጣኞች ማካፈል በሚችሉበት ሁኔታ ላይም ስልጠና እንደሚወስዱ ታውቋል።

በካፍ የአሰልጣኞች ፈቃድ አሰጣጥ ስርአት፣የአፍሪካን እግር ኳስ ያሳድጋሉ ተብለው በተቀረጹ ፕሮጀክቶችና ሌሎች የእግር ኳስ ልማት ስራዎች ላይ ገለጻ እንደሚደርግም ተጠቅሷል።

የካፍ የቴክኒክና ልማት ኮሚቴ 15 አባላት ያሉት ሲሆን በአፍሪካ እግር ኳስ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የሚሰራ የስራ ክፍል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም