ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የ56 የጤና ተቋማትን የክትትል ሪፖርት ይፋ አደረገ

58
አዳማ ግንቦት19/2010 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጤና መብት አጠባበቅ ዙሪያ በ56 የጤና ተቋማት ባደረገው ክትትል የታዩ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ ምክረ ሃሳብ አቀረበ ። በኮሚሽኑ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ትሁን ሽፈራው እንደገለፁት ኮሚሽኑ በስምንት  ክልሎች በሚገኙ  በእነዚህ የጤና ተቋማት ክትትል ያደረገው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ነው፡፡ ክትትሉ በደቡብ ህዝቦች ፣በሶማሌ ፣ በአማራ ፣ በትግራይ ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ፣ በአፋር ፣ በኦሮሚያና ጋምቤላ ክልሎች የተካሄደ ሲሆን 25 ሆስፒታሎች ፣ 16 ጤና ጣቢያዎችና 15 መካከለኛ ክሊኒኮች ያካተተ ነበር ። የክትትሉ  ዓላማ በሀገሪቱ የሚገኙ የህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገቢ ፣ ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ የሆነ፣  ፍትሃዊ ፣ ጥራትና የመክፈል አቅም የሌላቸውን ዜጎች ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው ። "በተለይ ለሴቶች፣ ህጻናት፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞችን ትኩረት በመስጠት የሀገሪቱን የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ዜጎች የጤና አገልግሎት የማግኘት መብታቸው በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለመፈተሽ ነው "ብለዋል ዳይሬክተሯ። የክትትሉ የመጨረሻ ሪፖርት ባለፉት ሁለት ቀናት በአዳማ ከተማ ባለድርሻ አካላትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት ለውይይት ቀርቧል ። በኮሚሽኑ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ሰለሞን ሹሙዬ ለመድረኩ ያቀረቡት የክትትሉ ሪፖርት እንደሚያመለክተው አብዛኛዎቹ የህክምና ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች በቂና አመቺ የሆነ መንሸራተቻ የላቸውም ። ከጥቂቶች በስተቀር ለአካል ጉዳተኞች ፣ ለነፍሰ ጡር እናቶች ፣ ለህፃናትና ለአቅመ ደካሞች በቅጡ መደገፊያ ያለው መፀዳጃ ቤቶች እንኳን ያላሟሉ ናቸው ። አብዛኛዎቹ በቂ አምቡላንስ ያላሟሉ ሲሆኑ ከነአካቴው የሌላቸው ጭምር እንዳሉ በክትትሉ መረጋገጡን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል። ፍላጎትን መሰረት ያላደረገ የመድኃኒት አቅርቦት አለመኖርና ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት በክትትሉ የታየ ክፍተት ሲሆን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግ ባለሙያ የሌላቸው ተቋማት ጥቂት አይደሉም ተብሏል ። የህክምና ባለሙያዎችም ቢሆኑ በበዓላትና በእረፍት ሰዓታቸው  ሰርተው የትርፍ ሰዓት ክፍያ የማያገኙበትና የዓመት እረፍት ጭምር ተሰጥቶአቸው የማያውቁ መኖራቸውን በክትትሉ ማረጋገጥ ተችሏል ። በርካታ ክፍተቶችን ነቅሶ ያወጣው የኮሚሽኑ የክትትል ሪፖርት ለማስተካከል የሚረዱ ምክረ ሃሳቦች ጭምር ያካተተ ሲሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲረባረቡ አሳስቧል ። በውይይት መድረኩ  የተሳተፉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰብአዊ ፣ ዴሞክራሲያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዳኜ በለጠ  በሰጡት አስተያየት" ኮሚሽኑ በክትትል የተመለከታቸው የአሰራር ክፍተቶች በአፋጣኝ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ቁልፍ ጉዳዮች በመሆናቸው ሁላችንም ጠንክረን ልንሰራበት ይገባል" ብለዋል ።     የአዳማ ጀነራል ሆስፒታልና ሜዲካል ኮሌጅ አስተዳዳሪ አቶ አበራ ብሩ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ድክመትን ብቻ ሳይሆን ጥንካሬም ጭምር በማሳያነት ያቀረበ ሪፖርት ይፋ ማድረጉ የህክምና ተቋማት እራሳቸውን እየፈተሹ ለተሻለ አገልግሎት እንዲተጉ የሚያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም