አካል ጉዳተኛ ህጻናት አምራችና ጤነኛ እንዲሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ

126

አዲስ አበባ ጥር 14/2011 አካል ጉዳተኛ ህጻናት ጤነኛና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጠየቁ።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በኪዩር ኢትዮጵያ የህጻናት ሆስፒታል 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ተገኝተው ማዕከሉን ጎብኝተዋል።

ከአገሪቷ ህዝብ 40 በመቶ የሚሆነው ከ15 ዓመት በታች መሆኑን በመጥቀስ በህጻናት ላይ በትኩረት መሰራት እንደሚገባ ጠቁመዋል ፕሬዝዳንቷ።

አብዛኞቹ አካል ጉዳተኛ ህጻናት ከማህበረሰቡ በሚደርስባቸው የስነ ልቦና ጫና የተነሳ ከትምህርት ቤት በመቅረት በቤተሰቦቻቸው ላይ ተደራራቢ ጫና እንዲደርስ ምክንያት ሆነዋል።

በዚህም ትምህርት ቤት በመሄጃ እድሜያቸው ቤት የሚውሉ ህጻናት በርካታ መሆናቸውን በመጥቀስ አምራችና ጤነኛ እንዲሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ይህንን ችግር ለማቃለል የህጻናትን የነገ ተስፋ ብሩህ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ በመጠየቅ ኪዩር ሆስፒታል እየሰራ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።

በተመሳሳይ በስልጠና፣ አቅም ግንባታና ህክምና ለሚሰማሩ ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በተለይም በገጠር አካባቢ የሚገኙ ህጻናት ተደራራቢ የጤና ችግር እንደሚያጋጥማቸው ጠቅሰዋል።

የኪዩር ኢትዮጵያ ህጻናት ሆስፒታል ዳይሬክተር ወይዘሮ አደይ አባተ ሆስፒታሉ ባለፉት 10 ዓመታት ከ17 ሺህ በላይ የተለያየ የአካል ጉዳት ላለባቸው ህጻናት ቀዶ ጥገና ማድረጉን ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከቅዱስ ጻውሎስ ሆስፒታል፣ ፈለገ ህይወትና ሌሎች መንግስታዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር እየሰራ መሆኑንም ተነግሯል።

ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ የአካል ጉዳት ያለባቸው ህጻናት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙና በአካል ጉዳታቸው ምክንያት የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍል ናቸው።

በሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት ያገኙ ህጻናት የአካል ጉዳት ችግር በነበረባቸው ወቅትና ህክምናውን ካገኙ በኋላ ያላቸውን የህይወት ልዩነት ተናግረዋል።

ኪዩር ኢትዮጵያ የህጻናት ሆስፒታል የጣት መጣበብ፣ የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ፣ የእሳት ቃጠሎና ሌሎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና ከ16 አመት በታች ለሆኑ ህጻናት የቀዶ ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ አለም አቀፍ ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም