በከተማው በተፈጠረ የጸጥታ ችግር በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

316

ሶዶ ጥር 14/2011 በወላይታ ዞን በጉኑኖ ሀሙስ ከተማ በተፈጠረ የጸጥታ መደፍረስ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በዞኑ የዶሞት ሶሬ ወረዳ መቀመጫ በሆነችው የጉኑኖ ሀሙስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ማጉጄ መጃ እንደተናገሩት ትናንት ምሽት ላይ በከተማዋ ረብሽ ተፈጥሮ ነበር፡፡

የጸጥታ ችግሩ የተከሰተው በከተማው ፖሊስና ባለሁለት ጎማ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪ ወጣቶች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

“በሞተር ሳይክሎች አማካይነት የሚፈጠሩ የስርቆትና ንጥቂያ ወንጀሎች በመበራከታቸው ችግሩን ለመፍታት ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አሽከርካሪዎቹ ያልተገባ ተግባር ፈጽመዋል” ብለዋል፡፡

እንደፖሊስ አዛዡ ገለጻ ከተፈቀደው በላይ የጫኑ ሞተረኞችን ለመቆጣጠር በተደረገ ጥረት አሽከርካሪዎቹ ተደራጅተው የፖሊስን ህግ የማስከበር ተግባር በማስተጓጎላቸው የህዝብ ጸጥታ ደፍርሷል፡፡

በተደራጀ መልኩ በወረወሩት ድንጋይም በንብረትና በሰው አካል ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በመንግስት ተቋማት ላይ ከፍተኛ የሆነ የንብረት ጉዳትና ውድመት መድረሱን የተናገሩት ኢንስፔክተር ማጉጄ የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ፣ የከተማዋ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት፣ ማዘጋጃ ቤትና የፖሊስ ጽህፈት ቤት ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡

“ከእዚህ በተጨማሪ አራት የመኖሪያና የሥራ ቤቶች መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል” ያሉት ኢኒስፔክተሩ፣ ለገበያ በመጡ የግለሰብ ተሽከርካሪዎች፣ በአምቡላንስና ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ተሽከርካሪ ላይም ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል፡፡

እንደ ፖሊስ አዛዡ ገለጻ በተፈጠረው ችግር የሰው ሕይወት አልጠፋም።

የአካል ጉዳት የደረሳቸው በርካታ ግለሰቦች በከተማው ጤና ጣቢያና በሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል የህክምና ክትትል በማድረግ ላይ ናቸው። 

በአደጋው የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የክልሉ ልዩ ኃይል ጣልቃ በመግባት የቁጥጥርና የማረጋጋት ሥራ መስራቱን ተናግረዋል፡፡

የከተማዋን ሰላም ለመመለስ በተደረገው ጥረት የአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጉን የገለጹት ኢንስፔክተር ማጉጄ ችግሩን ፈጥረዋል ተብለው የተጠረጠሩ ከ10 በላይ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማምጣትም ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ከታዋቂ ግለሰቦች ጋር በመሆን ህዝባዊ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ገልጸዋል፡፡