ዓመታዊው የአዲስ አበባ የወርልድ ቴኳንዶ ክለቦች ውድድር ከነገ በስቲያ ይጀመራል

72

ዓአዲስ አበባ   ጥር 14/2011 መታዊው የአዲስ አበባ የወርልድ ቴኳንዶ ክለቦች ውድድር ጥር 16 ቀን 2011 ዓ.ም በወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) የስፖርት ጅምናዚየም ይጀመራል።

በውድድሩ ላይ በአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፈቃድ የተሰጣቸው 30 ክለቦች የተወጣጡ 360 ስፖርተኞች ይሳተፋሉ።

በሁለቱም ጾታዎች ውድድሩ በተመሳሳይ በስድስት የክብደት ዘርፎች የሚካሄድ ሲሆን በወንዶች ከ54 እስከ 80 ኪሎ ግራም በሴቶች ከ46 እስከ 57 ኪሎ ግራም የነጻ ፍልሚያ ውድድሮች ይጠበቃሉ።

የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሃይሌ ጉተታ ለኢዜአ እንደገለጹት የውድድሩ አላማ ስፖርተኞች አቅማቸውን እንዲፈትሹና የውድድር አማራጮች ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ ነው።

በዚህ ውድድር ላይ አሸናፊ የሚሆኑት ተወዳዳሪዎች በአገር አቀፍ የወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ላይ መዲናዋን ወክለው እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት በመዲናዋ የወርልድ ቴኳንዶ ማሰልጠኛ ማዕከላት የሚገኙ ስፖርተኞች እንደሆኑና ማዕከላቱ በፌዴሬሽኑ የክለብ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ፌዴሬሽኑ በተያዘው በጀት ዓመት አገር አቀፍ የትምህርት ቤቶች ውድድርና አገር አቀፍ የፑምሴ (የአርት) ውድድር እንደሚካሂድም ጠቁመዋል። 

ዓመታዊው የአዲስ አበባ የወርልድ ቴኳንዶ ክለቦች ውድድር እስከ ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳል።

የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በ1995 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በመዲናዋ ስፖርቱን የማስፋፋትና የማደራጀት ሃላፊነትን ወስዶ በመስራት ላይ ይገኛል።

የኮሪያውያን የባህል ስፖርት በሚል የሚታወቀው ወርልድ ቴኳንዶ ከሰውነት ፍልሚያ ባሻገር ብዙ ጥበባዊ ይዘቶችን (ስልቶችን) በውስጡ ያካተተ ስፖርታዊ ክንዋኔ ነው።

አዕምሮንና ሰውነትን ማሰልጠን ጨምሮ ህይወትን በአግባቡ ለመምራት የሚያግዝ የስፖርት ዓይነት እንደሆነም በዘርፉ ያሉ ምሁራን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1970ዎቹ መዘውተር መጀመሩን መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን ስፖርቱን ለማሳዳግና ለማስፋፋት ሃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በ1995 ዓ.ም ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም